መጋቢት 6/2017 ዓ.ም
===============
የወራቤ ግብርና ምርምር ማዕከል በእኖር ወረዳ የድንች ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ለአርሶ አደሩ የቴክኖሎጂ ሽግግር እያደረገ መሆኑን የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት ገለጸ።
በወረዳው ወርቃት ቀበሌ በአርሶ አደሮች የድንች ማሳ በአማራጭ መስኖ ውሃ አጠቃቀም ላይ የመስክ ምልከታ ተካሄደ።
ጉብኝቱም በወራቤ ግብርና ምርምር ማዕከል በግብርና ቴክኖሎጂ ሽግግርና ግንኙነትና በሥርዓተ-ምግብ ማጠናከሪያ ፕሮግራም (FSRP)ገንዘብ ድጋፍ እየተሰራ ያለው አማራጭ የመስኖ ወሃ አጠቃቃምና የድንች ቴክኖሎጂ ስራ ላይ መሆኑንም ተጠቁሟል።
በመርሐ ግብሩ የተገኙት የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ አብድልመጂድ ጀማል እንደገለጹት የወራቤ ግብርና ምርምር ማዕከል ለወረዳው አርሶ አደሮችን ጉልበትና ወጪ በመቆጠብ ምርታማ መሆን እንደሚቻል ከፍተኛ እገዛ እያደረገ መሆኑን አውስተዋል።
በዚህም በአሁን ወቅት በድንች ሰብል ምርታማነት ላይ በተሰራው ስራ ለውጥ መኖሩን አመላክተዋል።
አርሶአደሩ በእጁ ያለው መሬት፣ውሃና የሰው ሀብት በተገቢው መጠቀም እንዳለበትም ኃላፊው አመላክተዋል።
የወራቤ ግብርና ምርምር ማዕከል ለወረዳው አርሶ አደሮች በቴክኖሎጂ በማገዝ የድንች ምርታማነት ለመጨመር እየሰራ ላለው ስራም አቶ አብዱልመጂድ በህዝቡ ስም አመስግነዋል ።
የወራቤ ግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ቢላል ተማም እንዳስታወቁት የምርምር ማዕከሉ በክልሉ በሚገኙ ዞኖችና ልዩ-ወረዳዎች ላይ በግብርና የምርምር ስራዎች ላይ ሙያዊ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል።
የምርምር ማዕከሉ የምግብ ዋስትናን ለመረጋገጥ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ ምርምሮችና ቴክኖሎጂዎች የማስተዋወቅ ሥራዎችን እየሰራ እንደምገኝ አስገንዝቧል።
የማዕከላዊ ኢትዮጲያ ግብርና ምርምር እንስቲትዩት በሥርዓተ-ምግብ ማጠናከሪያ ፕሮግራም ማናጀር አቶ ካሚል ተማም በበኩላቸው በወረዳው እየተሰራ ያለው የድንች ምርምር ስራ የምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጥ በመሆኑ ወደ ሌሎች አጎራባች አከባቢዎች ማሰፋት ይገባል ብሏል።
የምርምር ማዕከሉ በወረዳው በመስኖ እየለማ ላለው የድንች ማሳ ምርጥ ዘር ድንች ለአርሶአደሮች እንዳበረከተና ውጤታማ እንዲሆኑ ድጋፍና ክትትል እንዲሁም ለምርምሩ የሚያስፈልጉ መረጃዎችን በቅርበት ሆነው እየተከታታሉ መሆኑን ጠቁመዋል።
የምርምር ማዕከሉ አላማ አርሶአደሩ ውሀ፣ነዳጅ፣ገንዘብና ጉልበት ሳያባክን ወጪን በመቀነስ አዋጭነት ባለው መልኩ ሰርቶ በግብርናው ዘርፍ ውጤታማ በማድረግ የምግብ ዋስትናውን ከማረጋገጥ ባሻገር ገበያ ማረጋጋትና የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ ነው ብለዋል።
በቀበሌው በመስኖ ድንች የተሰማሩ ወጣቶች በጋራ በሰጡት አስተያየት ከማዕከሉ ባገኙት ስልጠና ግንዛቤ ቀደም ሲል ከነበረው ብክነት በመቆጠብ ምርታማ መሆን እንደሚቻል በተጨባጭ ማየት መቻላቸውን አመላክተዋል።
በአሁን ወቅት የምርምር ማዕከሉ ከወረዳው ግብርና ጽ/ቤት ጋር በመቀናጀት እያደረገላቸው ባለው የምርጥ ዘር፣የቴክኖሎጂና ሙያዊ ድጋፍ በተለይም በድንች መስኖ ውጤታማ ስለመሆናቸውም ተናግረዋል።
በጉብኝቱ ላይ ዘርፉን የሚመለከታቸው ኃላፊዎች፣ባለሙያዎችና አርሶአደሮች ተገኝተዋል


