የእኖር ወረዳ ጤና ፅ/ቤት ሀላፊ

ብርዝነሽ ባደታ ተረዳ

 

መግቢያ

የእኖር ወረዳ ጤና ጽ/ቤት ሀገራዊ  የጤና ፖሊሲን የሚያስፈጽም አጠቃላይ የጤና አገልግሎት ፓኬጅ በማቅረብና በመቆጣጠር ፍትሃዊ በሆነ መንገድ የህብረተሰቡን ጤና እና ደህንነት ለማስጠበቅ የተቋቋመ የመንግስት መስሪያ ቤት ሲሆን ተቋማዊ አወቃቀሩም ተጠሪነታቸው ለጽ/ቤቱ ዋና ሃለፊ የሆኑ 13 ዳይሬክቶሬቶች የተዋቀረና በስሩም አንድ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል፣ 8 ጤና ጣቢያዎች(6 የመንግስትና 2 የመያድ) እና 35 ጤና ኬላዎችን የሚያስተዳድር ተቋም ነው፡፡ በ2016 በጀት አመት ማብቂያ ላይ በአጠቃላይ 232 የጤና ሙያተኞች፣ 181 አስተዳደር ሰራተኞች እንዲሁም 60 የጤና ኤክስቴንሽ ሙያተኞች በጥቅሉ 473 ሰራተኞች ከወረዳው ጽ/ቤት ጀምሮ እስከ ቀበሌ ጤና ኬላ ድረስ ባሉ መዋቅሮች አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡

ከወረዳው ሕዝብ መካከል ሴቶች 51.4%፤ ወንዶች ደግሞ 48.6% እንደሆኑ ይገመታል፡፡ ከጠቅላላው ሕዝብ መካከል በመውለድ እድሜ ክልል (ከ15-49 የእድሜ ክልል) የሚገኙ ሴቶች 23.3%፣ ነፍሰጡር እናቶች 3.46%፣ በህይወት የሚወለዱ ህፃናት 3.46%፣ እድሜያቸው ከአንድ ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት 3.19%፣ ከሁለት ዓመት በታች 5.2%፣ ከአምስት ዓመት በታች 15.6% እና ከ15-45 ዕድሜ ክልል የሚገኙ 48.3% መሆኑን የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ስሌት ያሳያል፡፡

 

የወረዳው የጤና ሽፋን

 

የወረዳችንን የጤና ሽፋን ስንመለከት ለወረዳችን የመጀመሪያው የሆነው የጤና ተቋም የጉንችሬ ክሊኒክ ሲሆን ምስረታውም በ1967 በእድገት በህብረት ዘመቻ ነው፡፡ በ1976 ገደማ የወረዳው ሁለተኛ የጤና ተቋም የሆነው ወትራ ክሊኒክ አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡ በ1985 የወጣው ሃገራዊ የጤና ፖሊሲን ተከትሎ በ1989 የኩንችሬ ክሊኒክ ወደ ጤና ጣቢያነት አደገ አሱን ተከትሎ ወትራ ኪሊኒክም በ1991 ወደ ጃቱ ጤና ጣቢያ ከፍ አለ፡፡ በመሆኑም በ1990ዎቹ እነዚሁ 02 ጤና ጣቢያዎች ብቻ የነበሩ ሲሆን በአሁኑ ወቅት 1 የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታልና 8 ጤና ጣቢያዎች አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ ከ1997 ጀምሮ ደግሞ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም በመጀመር በሁሉም ቀበሌዎቻችን ጤና ኬላዎችን በመገንባትና የጤና ኤክስቴንሽን ሙያተኞችን በመቅጠር ለማህበረሰቡ ይበልጥ ቅርብ በመሆን የጤና አገልግሎቱን ይበልጥ ተደራሽ በማድረግ የበሽታ መከላከልና የፈውስ ህክምና አሰጣጡን ማሳለጥ ተችሎዋል፡፡ በመሆኑም አሁን ላይ የወረዳችን የመጀመሪያ ደረጃ የጤና አገልግሎት ሽፋን በ1990ዎቹ ከ50% በታች ከነበረበት 100% ማድረስ ተችሏል፡፡ በጤና ተቋም የነብስ ወከፍ የህክምና ተጠቃሚነት ምጣኔ በ2002 በጀት አመት ከነበረበት 0.53 በ2016 በጀት አመት ወደ 3.5 ማድረስ ተችሏል፡፡

 

 

የጤና ተቋሙ ስም

የጤና ተቋሙ የሚገኝበት ቀበሌ

በጤና ተቋሙ ስር ያሉ ሳተላይት ቀበሌዎች

በጤና ተቋሙ ስር ያሉ ጤና ኬላዎች ብዛት

ጉንችሬ መ/ደ/ሆ

ጉንችሬ

አሞገራ፣ጋሳውዴ፣ካሳይ፣ጋሃራድ

4

ተርሆኘ ጤ/ጣቢያ

ተርሆኘ

ተርሆኘ፣ጠረደ፣ኢባራኘ፣ወርቃት፣ሻፋሞ፣ጋዛንቸ፣አጫወደ

5

ጉስባጃይ ጤ/ጣቢያ

ጉስባጃይ

ሰንዲቃይ፣ወንጬ፣ጋርዳሼ፣እሰኸር፣ጓንታና፣ ጉስባጃይ ከተማ

4

ጃቱ ጤ/ጣቢያ

ጃቱ

ጃቱ፣አጋሬ፣ጎ/ቤቴ፣ገረንቦ፣ጎንደሬጨ ደንበር፣ጎምሸ፣ሆርበትዚዞ

8

አንዳሆረ ጤ/ጣቢያ

አንዳሆረ

አንዳሆረ፣ኮሰድ፣እናንገራ፣ሻንቃ፣ዳእምር፣እገበኝ

5

አጋታ ጤ/ጣቢያ

አጋታ

አጋታ፣ካናስ፣አቦጋዴ፣ኩነበር

4

ኧገዜ ጤ/ጣቢያ

እገዜ

እገዜ፣ጡማነ፣ወ/ዘውያር፣አዋስር፣እገዜ 01

3

ሸብራበር ጤ/ጣቢያ

ማቃና

መቃና፣ ከረቤድ

2

አቤኔዘር ጤ/ጣቢያ

ሁረድ

ሁረድ

0

የእናቶችና ህጻናት ሞት ምጣኔ

ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ሀገራችን ኢትዮጵያ በሴቶችና ህጻናት ጤና አገልግሎት ላይ ተጨባጭ ለውጥ አስመዝግባለች። ይህ ለውጥ በወረዳችንም በጉልህ የታየና ስኬታማ መሆኑን በግልጽ ታያቷል፡፡ እ.ኤ.አ በ2023 ተ.መ.ድ ባወጣው ሪፖርት መሰረት በኢትዮጲያ በ2020 የእናቶች ሞት ምጣኔ ከ100,000 267 እንደሚሞቱ መረጃው ያሳያል፡፡ ይህ ቁጥር በ2012 ከነበረው 401 የእናቶች ሞት ምጣኔ ከ100,000 አንጻር ሲታይ ከፍተኛ መሻሻል አሳይቷል፡፡

እንደ ወረዳችን ባለፉት አስር አመታት ወስጥ ከወሊድ ጋር በተያያዘ የተከሰተው የእናቶች ሞት ሶስት ሲሆን ይህም አበረታች ለውጥ መምጣቱን የሚያመላክትና የተሰሩ ስራዎች ውጤታማነት አረጋጋጭ ነው፡፡

እ/ኤ/አ በ2011 በተደረገው ሀገር አቀፍ ጥናት መሰረት የሀገራችን የጨቅላ ህጻናት ሞት 41/1000 መሆኑን ያሳያል:: ባለፉት አስር አመታት እንደ ወረዳችን 75 የጨቅላ ህጻናት ሞት የተመዘገበ ሲሆን ይህም በአስር አመቱ በህይወት ከተወለዱ ህጻናት አንጻር 1.5/1000 መሆኑን ያሳያል፡፡ በነዚሁ አመታት ውስጥ 151 ህጻናት ሞተው የተወለዱ ሲሆን በአጠቃላይ በህይወትና በሞት ከተወለዱት አንጻር 2.99/1000 ይሆናል፡፡ በከፍተኛ ደረጃ የጨቅላ ህፃናት ሞት መንስዔ የሆኑት፡- በተውሳኮች መመረዝ /infection/፣ የመተንፈሻ አካል መደፈን /asphyxia/ እና የመወለጃ ጊዜ ሳይደርስ መወለድ /prematurity/ ሲሆኑ ባለፉት አምስት ዓመታት በጤናው ሴክተር በዚሁ አቅጣጫ ትኩረት ሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል፡፡ የጨቅላ ህፃናት ፅኑ ህክምና አገልግሎት በጤና ተቋማትና በማህበረሰብ ደረጃ በጤና ኬላዎች በስፋት እየተስፋፉ ሲሆን ለማዋለጃ ክፍል የሚሆኑ መድሃኒቶችና የህክምና መገልገያ መሳሪያዎች የሟሟላት ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡ ይሁን እንጂ ጥራት ያለው አገልግሎት ክህሎት ባላቸው ባለሙያዎች ከመስጠት አኳያ ገና ብዙ ስራዎች ይጠበቃሉ፡፡

 

 

የቅድመ ወሊድ፣ ወሊድና ድህረ ወሊድ ሁኔታ

የወረዳችንን የቅድመ ወሊድ፣ ወሊድና ድህረ ወሊድ ሁኔታ ስንመለከት እስከ 2002 በጀት ዓመት ድረስ የቅድመ ወሊድ፣ የሰለጠነ ባለሙያ ወሊድና ድህረ ወሊድ አገልግሎት ከ10% ያልዘለለ ሲሆን ባለፉት አስር አመታት በፖለቲካውና ማህበራዊ ዘርፎች የተፈጠረውን መልካም አጋጣሚዎች በመጠቀም፣  የተዘረጋውን የጤና ልማት ሰራዊት ግንባታ በማጠናከርና አሟጦ በመጠቀም፣ አምቡላንሶች በአግባቡ በመጠቀም፣ ግብዓትና የሰለጠነ የሰው ኃይል በሟሟላት፣ የተሻሻሉ የጥራት ማረጋገጫ መመሪያዎችን በሁሉም ተቋማት ውስጥ ተግባራዊ እንዲሆኑ በማድረግ፣ የጤና መሰረተ-ልማት በሟሟላት እና የድገተኛ ቀዶ ጥገና አገልግሎትን በመስጠት የተሻለ አፈጻጸም እና ጥራት ለማስመዝገብ በየደረጃው ከፍተኛ ጥረት በማድረግ በ2016 በጀት ዓመት የቅድመ ወሊድ፣ የሰለጠነ ባለሙያ ወሊድና ድህረ ወሊድ አገልግሎትን ከ78 % በላይ ማድረስ ተችሏል፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣውን የህብረተሰቡን የጤና ፍላጎት ለማሟላት፣ በአገልግሎት ጥራት ላይ ያሉ ክፍተቶችን ለመፍታት፣ የጤና ባለሙያዎችን ቁጥር እና ስብጥር ለማሻሻል፣ የጤና ተቋማትን መሠረተ ልማትን ለማጠናከር፣ የማህበረሰብ ተኮር አደረጃጀት በጤና ላይ ያላቸውን ተሳትፎና ባለቤትነት ለማሻሻል፤ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም አመራርን ለማጠናከር እና የመረጃ ስርዓት ማሻሻልን ጨምሮ ለማመቻቸት በቀጣይም በርካታ ስራዎች መሰራት ይኖርባቸዋል፡፡

 

በወረዳችን ለጤና ስጋት ይሆናሉ ተብለው የተለዩ ዋና ዋና ጉዳዮች

  • እጅግ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት፣
  • የህበረተሰቡ የኢኮኖሚ ደረጃ ዝቅተኛ መኖር
  • የህብረተሰቡ የጤና እና የጤና ስርዓት ዕውቀት ዝቅተኛ መሆን፣
  • ጤናማ ያልሆነ አኗኗር፣ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እና የጤና ጉዳት ተገላጭነት መጨመር፣
  • የማህበረሰብ መሰላቸት (ምሳሌ ጤና ልማት ሰራዊት)
  • የሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች መጨመር
  • የድንገተኛ አደጋዎችና የበሽታዎች ወረርሽኝ መከሰት፣
  • ዝቅተኛ የመሰረተ ልማት መኖር (መንገድ፣ የውሃ አቅርቦት፣ የኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ፣ አሌክትሪክ ወዘተ..)
  • የአገልግሎት አቅርቦትን የሚያደናቅፉ አለመረጋጋቶች እና ግጭቶች መከሰት፣
  • ዝቅተኛና ያልተገመተ የፋይናንስ አቅርቦት መኖር፣
  • የአየር ንብረት ለውጥና የሙቀት መጨመር፣
  • የሕገ-ወጥ የምግብ እና የመድኃኒት ምርቶች ቁጥጥር ደካማ መሆን፣
  • ደረጃቸውን ያልጠበቁ የመጠጥና የምግብ ምርቶች መኖር
  • በቂ የሆነ የግብዓት አቅርቦት አለመኖር
  • የአለም ኢኮኖሚ የዋጋ ግሽበት በመድሃኒቶች፣ በህክ/መገ/ መሳሪያዎችና በላብራቶሪ አቅርቦቶች ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ መኖሩ፤
  • አዲስና ነባር የሆኑ በሽታዎች በወረርሽኝ መልክ መከሰታቸው

የኤች.አይ.ቪ/ ኤድስ ሁኔታ

እ.ኤ.አ. በ2025 ሶስቱን 95-95-95 የኤች.አይ.ቪ ዒላማዎች ለማሳካት አበረታች ለውጥ ተመዝግቧል። በአሁኑ ወቅት 221 ኤች.አይ.ቪ. በደማቸው ያለባቸው ሰዎች የጸረ-ኤች.አይ.ቪ መድሃኒት እየወሰዱ ይገኛሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ 61 ወንዶች ሲሆኑ የተቀሩት 160ዎቹ ደግሞ ሴቶች ናቸው፡፡ በእድሜ ደረጃ ስንመለከት ከ15 አመት በታች 4 ህጻናት ፣ከ15 -29 አመት እድሜ 26 ሰዎች፣ ከ30-44 አመት እድሜ 77 ሰዎች እና ከ45 አመት በላይ 114 ሰዎች የጸረ-ኤች.አይ.ቪ መድሃኒት እየወሰዱ ይገኛሉ፡፡ በወረዳችን በአሁኑ ጊዜ ኤች.አይ.ቪ በደማቸው ይኖርባቸዋል ተብሎ ከሚጠበቀዉ ሰዎች መካከል 89% የሚሆኑት ኤች.አይ.ቪ እንዳለባቸው ያወቁ ሲሆን ከነዚህ መካከል 100% ያህሉ የጸረ ኤች.አይ.ቪ መድኃኒት መጠቀም የጀመሩ መሆኑ እና መድኃኒት ከጀመሩት መካከል 98% የሚሆኑት በደማቸው ውስጥ የሚገኘው የቫይረስ መጠን መቀነሱ ታውቋል:: ከጠቅላላው ቫይረሱ በደማቸው ከሚኖርባቸው የህብረተሰብ ክፍል አንጻር ሲታይ የጸረ ኤች.አይ.ቪ መድኃኒት ተጠቃሚነት ሽፋን 91% ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 95% የሚሆኑት የቫይረስ መጠኑ እንዳይራባ ባለበት እንዲቆም የተደረጉ ናቸው።

በተለያዩ ጊዜያት የሚወጡ የቅኝት ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት በ2007 ዓ.ም የወረዳችን የቫይረሱ ስርጭት 0.01% የደረሰ መሆኑን እና ቫይረሱ በደማቸው ያለባቸው ሰዎች መጠን /ፐርቫልነች/ በ 2003 ከነበረበት 0.11% በ2016 በጀት አመት ወደ 0.06% ዝቅ ማለቱን ያሳያሉ፡፡

 

የጤናው ሴክተር ራዕይ፣ ተልዕኮና እሴቶች 

ራዕይ

ጤናማ፣ አምራች እና የበለፀገ ህብረተሰብ ተፈጥሮ ማየት ሲሆን

ተልዕኮ

ጥራቱን የጠበቀ፤ ፍትሐዊና ተደራሽ የሆነ የተሟላ የጤና አገልግሎት በመስጠት እና በሽታዎችን በመከላከል እና በመቆጣጠር የህዝቡን ጤና እና ደህንነት መጠበቅ ነው።የጤናውን ዘርፍ ተልዕኮ ለማሳካት የሚከተሉት

እሴቶች

  ቅድሚያ ለማህበረሰብ መስጠት፣ ተባባሪነት፣ ሩህሩህነት፣ ሙያ አክባሪነት፣ ሚስጥር ጠባቂነት፣ ህግ አክባሪነት እና አለማዳላት ናቸው። እንዲሁም የጤና ስርዓቱ መርሆዎች ጥራት፣ ፍትሃዊነት፣ ተጠያቂነት፣ ግልፀኝነት፣ ቀጣይነት፤ ትምህርት ላይ የተመሰረተ እና ቀልጣፋ አገልግሎት አሰጣጥ ናቸው።

 

የጤናው ሴክተር ዋና ዋና ግቦች

  • የእናቶች፤ የጨቅላ ህጻናት ህጻናት፤ አፍላ አፍላ ወጣቶች ጤና እና ስነ- ምግብ ሁኔታ ማሻሻል
  • የበሽታዎች መከላከል እና መቆጣጠር ማሻሻል
  • የማህበረሰብ ባለቤትነትን እና የመጀመሪያ ደረጃ የጤና እንክብካቤን ማሻሻል
  • ጥራት ያለው እና ፍትሃዊ የህክምና አገልግሎት ተደራሽነትን ማሻሻል
  • የድንገተኛ አደጋዎች ቁጥጥር፤ መከላከል እና መልሶ ማቋቋም
  • ጤና ስርዓት አቅም እና ቁጥጥርን ማሻሻል
  • አዳዲስ የፈጠራ ዘዴን ለጤና ስርዓት ጥራት፣ ፍትሃዊነት እና ደህንነት
  • የመድኃኒት እና የህክምና መሳሪያዎች አያያዝ እና ምርትን ማሻሻል
  • የጤና ፋይናንስ እና የግሉ ዘርፍ ተሳትፎን ማሻሻል