ወንጀልን አለማሳወቅ ወንጀል መሆኑን ያውቃሉ?
የቅርብ ዘመድ ወይም ወዳጅ ወንጀል መፈፀሙን ብታውቁ ለሕግ አሳልፋችሁ ትሰጡታላችሁ ወይስ ዝምድናው ወይም ወዳጅነቱ ይዟችሁ አይቶ እንዳላየ ሆናችሁ ትደብቃላችሁ? ጉዳዩ የህሊና እንዲሁም የሕግ ተጠያቂነትን የሚመለከት ነው። የህሊናውን ለየራሳችን ትተነው ሕጉ ምን እንደሚል እንይ።
በሞት ወይም በዕድሜ ልክ እስር ሚያስቀጣ ወንጀል
በወንጀል ሕጋችን አንቀፅ 443 ላይ ማንኛውም ሰው በቂ ምክንያት ከሌው በስተቀር በሞት ወይም በእድሜ ልክ የሚያስቀጣ ወንጀል መፈፀሙን ወይም የፈፃሚውን ማንነት እያወቀ ለሚመለከተው አካል (ለፖሊስ) ሳያሳውቅ ከቀረ ወንጀልን ባለማሳወቅ ወንጀል ይቀጣል። ይህ ሕግ ማናችንም ላይ የተጣለብን ግዴታ ነው።
ሙያዊ ኃላፊነት ያለበት ሰው
ሌላኛው ወንጀልን ለሕግ አካል የማሳወቅ ግዴታ የሚመነጨው ደግሞ ግለሰቡ ከተሰማራበት የሙያ ግዴታ ሲሆን ከዚህ አይነት ሙያዎች መከከል ለምሳሌ የጥበቃ፣የፍተሻ፣የመቆጣጠር፣ፍቃድ የመስጠት የመሳሰሉት ሙያዎች መጥቀስ ይቻላል። በነዚህ ሙያዎች ላይ የተሰማሩ ሰዎች ለህብተረተሰቡ ሰላምና ደህንነት አስጊ የሆኑ ወንጀሎችን ወይም ከባድ ሁኔታዎችን የማሳወቅ ግዴታ ያለባቸው ሲሆን የሙያ ግዴታቸውን በመጣስ ወይም በምንቸገረኝ ወንጀሉን ለሚመለከተው አካል ካላሳወቁ እሰከ ብር 1000 ወይም እስከ 6 ወር እስራት ሊያስቀጣቸው ይችላል።
በተለይም ደግሞ ከፍተኛ አደጋ በሚፈጥሩ የተወሰኑ የወንጀል አይነቶች ላይ ወንጀልን አውቆ አለማሳወቅ የሚያስከትለው ሀላፊነት ከፍ ያለ ነው። ከነዚህ መሀል ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው።
የሀገርና የሕዝብ ደህንነትን ሚመለከት ወንጀል
በሕገመንግስታዊ ስርዓቱ፣ በሉአላዊነታችን፣ በመከላከያ፣ በውስጥና በውጭ ደህንነታችን ላይ የተሞከሩ፣ የተሰናዱ፣ የተፈፀሙ ወንጀሎችን አውቆ አለማሳወቅ፣ አደጋው፣ አንዳይደርስ ወይም አድራሹ እንዳይያዝ የሚችለውን ያላደረገ ሰው ከአቅም በላይ በሆነ ወይም ግልፅ ምክንያት ግዴታውን ሳይወጣ መቅረቱን ካላስረዳ በወንጀል ይቀጣል።
በወንጀል ሕጉ አንቀፅ 254 መሰረት ቅጣቱ ከ5 አመት የማይበልጥ ፅኑ እስር ሲሆን ወንጀሉ የተፈፀመው ያገራችን የውስጥ ወይም የውጭ ደህንነት አስጊ ሁኔታ ላይ ሆኖ ከሆነ ቅጣቱ እስከ 10 ዓመት ፅኑ እስር ይደርሳል።
ወታደራዊ ኩብለላ ወይም አመፅ
ወታደራዊ ኩብለላ ወይም አመፅ መዘጋጀቱን ወይም መፈፀሙን አውቆ ለሚመለከተው አካል ሳያሳወቁ መቅረት ፣እንዳይፈፀም ማድረግ ወይም አድራጊው አንዲያዝ አቅም የፈቀደውን አለማድረግም በቂ ምክንያት ከሌለ በቀር ያስቀጣል። በወንጀል ሕጉ አንቀፅ 335(1) መሰረት ቢያንስ ወንጀሉ ከተሞከረ በቀላል እስራት ነገሩ ከባድ ከሆነ ደግሞ ከ3 ዓመት ማይበልጥ ፅኑ እስር ያስቀጣል።
የሽብር ወንጀል
በሽብርተኝነት አዋጁ 1176/2012 አንቀጽ 15 መሰረት የሽብር ድርጊት፣የሽብር ወንጀል ለመፈፀም ማቀድና መሰናዳትን፣የሽብር ወንጀል ለመፈፀም ማደምን፣ለሽብር በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ ድጋፍ የማድረግ ተግባርን፣ለሽብር የማነሳሳትና ከሽብር ወንጀል ጋር የተገናኘ ንብረት የመያዝ ወንጀሎች አንዱ ሊፈፀም፣እየተፈፀመ ወይም የተፈፀመ መሆኑን ወይም የወንጀል ፈፃሚውን ማንነት እያወቀ በቂ ምክንያት ሳይኖረው ወዲያውኑ ለፖሊስ ወይም አግባብ ላለው የሕግ አስፈፃሚ ካላሳወቀ ከአንድ አመት እስከ ሦስት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ይቀጣል።
የሽብር ወንጀልን ያለማሳወቅ ቅጣቱን የሚያከብደው ደግሞ የሚያውቀውን መረጃ አሳውቆ ቢሆን ኖሮ ወንጀሉን መከላከል ወይም ማስቀረት የሚቻል ዓይነት ከሆነ ቅጣቱ ከሦስት እስከ ሰባት ዓመት የሚደርስ ጽኑ እስራት ይሆናል።
በሽብር ድርጊት የተጠረጠረን ወይም የተከሰሰን ሰው አስቀድሞ በማስጠንቀቅ፣በመደበቅ ወይም ዱካውን በመሸሸግ ወይም በማጥፋት፣የሚደረግ ምርመራን በማሳሳት ወይም በሌላ በማናቸውም መንገድ ተከሶ እንዳይቀርብ የረዳ ከሆነ ከሦስት እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ይቀጣል።ይህ ያለማሳወቅ ወይም በሽብር የተጠረጠረ ሰውን ተከሶ ለሕግ እንዳይቀርብ የመርዳት ድርጊት የወንጀል ተጠርጣሪውን መያዝ ወይም ማስቀጣት ቢቻልም እንኳን የሽብር ወንጀልን የማሳወቅና በሽብር የተጠረጠረ ሰውን በማንኛውም መንገድ በሕግ እንዳይጠየቅ ያለመርዳት ግዴታውን ያልተወጣ ሰው ለጥፋቱ መቀጣቱ እንደማይቀርለት አዋጁ ይደነግጋል።
ይህ የየሽብር ድርጊቶችን የማሳወቅ ኃላፊነት በሕግ ሚስጥር የመጠበቅ ግዴታ ያለባቸው ሰዎች ላይ ተፈፃሚ የማይሆን ሲሆን ወንጀሉ ሊፈፀም ወይም እየተፈፀመ ያለ ስለመሆኑ መረጃ ያለው ሰው ግን ይህን መብት ወይም ግዴታ እንደመከላከያ ሊያቀርብ አይችልም። ሚስጥር የመጠበቅ ሙያዊ ግዴታ የሽብር ወንጀልን ካለማሳወቅ ተጠያቂነት ሊያድን ሚችለው የሽብር ድርጊቱ የተፈፀም ወይም ድርጊቱ ካለፈና ጉዳቱን ለማስቀረት ወይም ለመከላከል ማይቻል ከሆነ ብቻ ነው።
ወንጀልን ላለማሳወቅ በቂ ሚባል ምክንያት
ወንጀልን አለማሳወቅ ከላይ በተጠቀሱት ሁኔታዎች ውስጥ እንደሚያስቀጣ አንስተናል። ሆኖም ግለሰቡ ወንጀሉን ያላሳወቀው ‘‘በቂ ምክንያት’’ ኖሮት ከሆነ ላያስቀጣው እንደሚችል አይተናል።
“በቂ ምክንያት” የሚባለው ግለሰቡ ወንጀሉን ያላሳወቀው ‘‘ራሱን፣የቅርብ የስጋ ወይም የጋብቻ ዘመዱን ወይም በተለይም በጥብቅ ወዳጅነት የተሳሰረውን ሰው ለቅጣት ፣ለውርደት ወይም ለከባድ አደጋ ላለማጋለጥ’’ ከሆነ ነው። ከላይ የጠቀስነውን ወንጀልን ለሕግ አካል ያለማሳወቅ ምክንያት ከወንጀሉ አደገኛነትና ከሌሎችም ሁኔታዎች አንፃር መዝኖ በቂ ሆኖ ካገኘው በወንጀል ሕጋችን አንቀፅ 83(1) መሰረት ፍርድ ቤቱ ወንጀሉን ባለማሳወቅ ክስ የቀረበበትን ሰው ቅጣቱን በመሰለው መልኩ ያቀልለታል ወይም ከመነሻው የቅጣት መጠን ዝቅ አድርጎ ሊቀጣው ወይም ቅጣቱን በቀላል ሌላ ቅጣት ሊተካለት ይችላል።
ወዳጅነቱ ወይም ዝምድናው ከሚያስጠይቀው ወንጀል ክብደት ጋር ሲነፃፀር በጣም ጥብቅ ከመሆኑ የተነሳ ጭንቀት ፈጥሮበት ወንጀሉን ሳያሳውቅ የቀረን ሰው ፍ/ቤቱ በወቀሳ ወይም በማስጠንቀቂያ ሊያልፈው ይችላል።
