በእኖር ወረዳ ከ10 ሺ 500 ሄ/ር መሬት በላይ በተቀናጀ ተፋሰስ ልማት ስራ በተለያዩ ስትራክቸሮች ማልማት መቻሉን የእኖር ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት አስታወቀ

መጋቢት 1/2017 ዓ.ም
================በእኖር ወረዳ ከ10 ሺ 500 ሄ/ር መሬት በላይ በተቀናጀ ተፋሰስ ልማት ስራ በተለያዩ ስትራክቸሮች ማልማት መቻሉን የእኖር ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት አስታወቀ።
የ2017 ዓ.ም የተቀናጀ ተፋሰስ ልማት ስራ የመዝጊያ ፕሮግራም በወረዳው ኮሰድ ቀበሌ ተካሂዷል።
የእኖር ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ አብድልመጅድ ጀማል በመዝጊያ ፕሮግራም ላይ ተገኝተው እንደገለፁት የተቀናጀ ተፋሰስ ልማት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት ጉልህ ሚና እንዳለው ገልፀዋል።
በወረዳው በሁሉም ቀበሌዎች ከጥር 26/2017 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ 25 ቀናት እየተከናወነ የነበረው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሞዴል ስራ መሰራቱን አስረድተዋል።
እንደ ሀላፊው ገለፃ እንደ ወረዳ በ2017 ዓ.ም 10,599 ሄ/ር መሬት በተቀናጀ ተፋሰስ ልማት ስራ ለማልማት ታቅዶ ከ10 ሺ 500 ሄ/ር መሬት በላይ በተለያዩ ስትራክቸሮች ማልማት መቻሉንም አብራርተዋል።
ለዚህም ሁሉ መሳካት በአምና ደረጃ የተለዩ ጉድለቶች ለአብነትም የሰዓት መሸራረፍ ፣የሴቶችና የወጣቶች ተሳትፎ ውስንነት በዘንድሮ ዓመት እንዲሻሻሉ በማድረግ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራው በተሳካ ሁኔታ ተከናውኗል ያሉ ሲሆን በቀጣይም የበልግ ልማት ስራዎችን በማጠናከር የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ማሳደግ ይገባልም ብለዋል ።
አጠቃላይ የግብርና ልማት ስራዎች ከተፋሰስ ልማት ስራ ጋር ሰፊ ቁርኝት ያላቸው መሆኑን ጨምረው የገለፁት አቶ አብድልመጅድ ይህንኑ ዘላቂ እንዲሆን በስነ ህይወታዊ ስራዎች ለአብነትም ከመኖ እና ከፍራፍሬ ልማት በማስተሳሰር እንዲሁም እንደ ወረዳ እየተስተዋለ የሚገኘውን አሲዳማ መሬትን በማከምና ከተፋሰስ ልማት ተግባር ጋር አቀናጅቶ መምራት የሚጠይቅ መሆኑንም አስገንዝበዋል ።
የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት ምክትልና የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ልማት ዘርፍ ሐላፊ አቶ ከድር አብድላ በበኩላቸው በወረዳው በተለዩ 40 ንዑስ ተፋሰሶች ከ10,501 ሄ/ር መሬት በላይ እንደየአካባቢው አግሮኢኮሎጂ ቀጠና የተመረጡ የስነ አካላዊ የአፈርና ውሃ መጠበቂያ ስትራክቸሮችን ተግባራዊ መደረጉን ተናግረዋል።
በወረዳው ለተከታታይ 25 ቀናት ተግባራዊ በተደረገው የተፋሰስ ልማት ላይ በአጠቃላይ ከ48ሺ በላይ የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች መሳተፋቸውን ሐላፊው ጠቁመዋል።
በዚህም በስነ ህይወታዊ ልማት ስራዎች በወረዳው በሁሉም ቀበሌዎች የመንግስት እና የማህበረሰብ ችግኝ ጣበያ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን መዘጋጀታቸውንም አንስተዋል።
በመዝጊያው ፕሮግራም ተሳታፊ ከሆኑት መካከል አቶ አወል ናስር፣አቶ ህትት አስፋ እና ወ/ሮ ጀሚላ ሙባሪክ በሰጡት አስተያየት በዘንድሮው የተፋሰስ ልማት ስራ በተፈጥሮ በተጎዳ መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ መስራታቸውና በቀጣይም በስነ ህይወታዊ ስራ ለማጠናከር በትኩረት እንደሚሰሩ አመላክተዋል።
አክለውም ቀደም በተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ፕሮግራም በለሙ መሬቶች የአካባቢው ለምነት፣የገፀና የከርሰ ምድር ውሃ እንዲሁም የግብርና ምርትና ምርታማነታቸው መጨመር መቻሉን አስታውቀዋል።
በመጨረሻም በአጠቃላይ በ2017 ዓ.ም በተቀናጀ ተፋሰስ ልማት አፈፃፀም ግንባር ቀደም ለሆነው ኮሰድ ቀበሌ፣በቀበሌው ውስጥ ያሉ አደረጃጀቶች፣የሴቶችና የወጣቶች የልማት ቡድኖች የማበረታቻና እውቅና ሰርተፊኬት ተበርክቶላቸዋል::

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *