በእኖር ወረዳ በ (FSRP) በስርአተ ምግብ ማሻሻያና ማጠናከሪያ ፕሮግራም የህብረተሰቡን ዘላቂ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ አበረታች የልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተገለጸ።
በወረዳው በፕሮግራሙ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት በአስተባባሪ አመራር፣በወረዳው ምክር ቤት አፈ ጉባኤና ቋሚ ኮሚቴ ተጎብኝተዋል።
በዘመናዊ መልክ ደረጃውን ጠብቆ እየተገነባ ያለው የማቃና ችግኝ ማባዣ ጣቢያ፣የጃቱ ኩሬ ውሃ በመጠቀም እና የናይካቭ ወንዝ በሶላር ሃይል በመጠቀም እየተሰራ ያለው የአጋሬና የጃቱ ወጣቶች መስኖ ልማት ተሳታፊዎች ተዟዙረው ተመልክተዋል።
በፕሮግራሙ እየተገነቡ የሚገኙ አጉስባጃይ የገበያ ማዕከል፣የሲከምሰር አንጓረ ድልዲይ ፣የጃቱ አጋሬ የናይካቭ ወንዝ ድልዲይ፣የሆርበት ዚዞ ኩሬ ቁፋሮና የጃቱ ኩሬ ጥገናም በተሳታፊዎቹ ተጎብኝተዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ተሳታፊዎች ግንባታቸው የተጠናቀቁ የጎንቸቤቴና የጃቱ ኩሬዎች፣የጎንቸቤቴ የእንስሳት በረት፣አጋሬ በመስኖ ስራ ላይ ለተሰማሩ ወጣቶች የናይካቭ ወንዝ ውሃ እንዲጠቀሙ የተገጠመውን የሶላር አገልግሎትም ተመልክተዋል።
በመስክ ምልከታው ላይ የተገኙት የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ መብራቱ ተክሌ በወረዳው በ (FSRP) በስርአተ ምግብ ማሻሻያና ማጠናከሪያ ፕሮግራም የህብረተሰቡን ዘላቂ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ አበረታች የልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
ፕሮግራሙ በወረዳው በተለይም በምግብ ሰብል እራስን ለመቻል እየተደረገ ባለው ጥረት የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
ለመስኖ ስራ አገልግሎት የሚውሉ ኩሬዎችን በመቆፈር፣ በርካታ ጠቀሜታ ያላቸው የውሃ መሳቢያዎችና የመሳሉትን እያበረከተ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ከምግብ ፍጆታ ባሻገር ትርፍ አምራች አርሶ አደሮችና ወጣቶች የገበያ ትስስር በመፍጠር ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ በወረዳው እየተሰራ ያለውን ስራ ከጎን ገብቶ በማገዝ ድልዲዮችና የገበያ ማዕከላት በመገንባት ትውልድ ተሻጋሪ አሻራውን እያኖረ እንደሚገኝም ዋና አስተዳዳሪው ገልጸዋል።
በጃቱና አጋሬ አካባቢ በፕሮግራሙ እየተገነባ ያለው የናይካቭ ወንዝ ድልዲይ የአካባቢው ህዝብ የዘመናት ጥያቄ ምላሽ የሰጠ ነው ብለዋል አቶ መብራቱ።
በአጠቃላይ ፕሮግራሙ እያደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የጠቆሙት ዋና አስተዳዳሪው ከፍተኛ ምስጋናም አቅርበዋል።
የወረዳው ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ የተከበሩ አቶ መህዲ አህባብ በበኩላቸው በፕሮግራሙ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ከፍ የሚያደርጉና ለቀጣይ ትውልድ የሚሸጋገሩ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።ለዚህም ምስጋና ይገባዋል ብለዋል።
ይህንን ምቹ ሁኔታ በመጠቀምና የህብረተሰቡ የስራ ባህል በማጠናከር ድህነትን ለማሸነፍ መረባረብ እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል አቶ መህዲ።
የወረዳው የስርአተ ምግብ ማሻሻያና ማጠናከሪያ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ጌቱ ኮራ የመስክ ምልከታውን በመምራት እየተከናወኑ ባሉ ተግባራት ዙሪያ ለተሳታፊዎች ተጨማሪ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ፕሮጀክቶቹ ለህብረተሰቡ ዘላቂ ጥቅም እንዲሰጡ ከፍተኛ የሆነ የክትትልና የቁጥጥር አሰራር በመዘርጋት ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል አቶ ጌቱ።
ፕሮግራሙ እያከናወነው ባለው ተግባር ህብረተሰቡ የበለጠ ተጠቃሚ እንዲሆን የተገነቡ ድልዲዮች በመንገድ ማስተሳሰርና ለመስኖ ልማት ልዩ ትኩረት መስጠት እንደሚገባም አቶ ጌቱ አስገንዝበዋል።
ተሳታፊዎች በፕሮግራሙ ድጋፍ እየተሰሩ ባሉ የልማት ስራዎች መደሰታቸውን ጠቁመው ለፕሮግራሙ ውጤታማነትና ለህብረተሰቡ ተጠቃሚነት የድርሻቸውን እንደሚወጡም ገልጸዋል





