በጉራጌ ዞን የእኖር ወረዳ ፍርድ ቤት ከጥቅምት 3/2018 ዓ.ም ጀምሮ የበጀት አመቱን የተሟላ የዳኝነትና አስተዳደራዊ ስራዎች አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ገለጸ

በጉራጌ ዞን የእኖር ወረዳ ፍርድ ቤት ከጥቅምት 3/2018 ዓ.ም ጀምሮ የበጀት አመቱን የተሟላ የዳኝነትና አስተዳደራዊ ስራዎች አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ገለጸ።
እንደ ፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት አቶ አሰፋ በረከት ገለጻ የማዕከላዊ ኢ/ያ ክልል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 01/2016 መሰረት ለሁለት ወራት ማለትም ከነሐሴ 1/2017 ዓ.ም እስከ መስከረም 30/2018 ዓ.ም ድረስ የፍርድ ቤቶች ስራ በከፊል ዝግ ሆነው የሚቆዩ መሆኑን ይደነግጋል።
ይህንንም መነሻ በማድረግ ዳኞች እረፍት ሊወጡ እንደሚችሉ የዳኝነት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 02/2016 አንቀጽ 39(1) ላይ በተደነገገው መሰረት የእኖር ወረዳ ፍርድ ቤትም ላለፉት ሁለት ወራት በከፊል ዝግ ሆኖ መቆየቱን ፕሬዚዳንቱ አስታውሷል።
ይሁን እንጂ የአስቸኳይነት ባህሪ ያላቸው የእጅ ከፍንጅ ወንጀሎች፣የጊዜ ቀጠሮ፣የእምነት ቃል የመሪ ትዕዛዝ ይሰጥልኝ፣
የመያዣና የብርበራ ትዕዛዞች ፍርድ ቤቱ ተቀብሎ ሲያከናውን እንደነበር ጠቁሟል።
ስለሆነም ከጥቅምት 3/2018 ዓ.ም ጀምሮ የበጀት አመቱን የተሟላ የዳኝነትና አስተዳደራዊ ስራዎች አገልግሎት መስጠት መጀመሩን የፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት አቶ አሰፋ በረከት ገልጿል።
ፕሬዚዳንቱ የ2018 ዓ.ም የ1ኛው ሩብ አመት የጸጥታ መዋቅር ተግባር አፈጻጸም በወረዳው ፍርድ ቤት አዳራሽ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የዜጎች ቻርተር ውይይት መድረክ መርቷል።
በዕለቱም የፍርድ ቤት፣የፍትህ ጽ/ቤት፣የሰላምና ጸጥታ ጽ/ቤት፣የፖሊስ ጽ/ቤት እና የሚሊሻ ጽ/ቤት ተግባር አፈጻጸም ሪፖርት በሐላፊዎች በኩል ቀርቦ ተገምግሟል።
በውይይቱም ተሳታፊዎች ለቀጣይ ተግባር ግብአት የሚሆኑ በሳልና ገንቢ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ያቀረቡ ሲሆን ከሐላፊዎችና ከመድረኩ ተጨማሪ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል።
በፕሮግራሙ ላይ የወረዳው ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ክብርት ፈቲሃ ዮሐንስ፣የህግ ፍትህና መ/አ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ትዛዙ ለማን ጨምሮ የፀጥታ መዋቅር ሐላፊዎችና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *