አሁን የደረስንበት የድጅታል አለም ተጽዕኖ ለማሸነፍ ጠንክሮ ከመማር ውጪ የተሻለ አማራጭ እንደሌለ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ገለጹ።

ታህሳስ 16/2018 ዓ.ም
===============አሁን የደረስንበት የድጅታል አለም ተጽዕኖ ለማሸነፍ ጠንክሮ ከመማር ውጪ የተሻለ አማራጭ እንደሌለ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ገለጹ።
አምባሳደሩ ይህን የገለጹት በዛሬው ዕለት የእኖር ወረዳ አስተባባሪ አመራር በተገኙበት ለሸብራበር 1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪዎች የዩኒፎርም አልባሳት ድጋፍ ባደረጉበት ወቅት ነው።
የምስጋናው ፋውንዴሽን የበላይ ጠባቂ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ እንደተናገሩት አሁን የደረስንበት የድጅታል አለም ተጽዕኖ ለማሸነፍ ጠንክሮ ከመማር ውጪ የተሻለ አማራጭ እንደሌለ በማወቅ ተማሪዎች ከወዲሁ ራሳቸውን በዕውቀት እንዲያዘጋጁ አሳስበዋል።
እንደ አምባሳደሩ ገለጻ የትምህርት ግብአት ከተሟላ፣የትምህርት አመራርና መምህራን በአግባቡ ከተጉ እንዲሁም ወላጅ የበኩሉን ከተወጣ ውጤት ማስመዝገብ የተማሪ ድርሻ ነው ብለዋል።የበለጸጉ አገሮች የእድገታቸው ሚስጥር ትምህርት/ዕውቀት እንደሆነም ጠቅሰዋል።
በመሆኑም ተማሪዎች ለትምህርታቸው ልዩ ትኩረት በመስጠት የወደፊቱ ህይወታቸውን ማስተካከል እንዳለባቸው አምባሳደሩ ልምዳቸውን በማካፈል መክረዋል።
የተማሪ ወላጆች በግብርናው ዘርፍ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር ከሚያደርጉት ጥረት ጎን ለጎን ልጆቻቸው በዕውቀትና በጥሩ ስነ ምግባር ተኮትኩተው እንዲያድጉ ማበረታታት እንዳለባቸውም አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ አስገንዝበዋል።
የወዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ መብራቱ ተክሌ በበኩላቸው በወረዳው የትምህርት ጥራትና የተማሪ ውጤት ለማሻሻል ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።ለተግባራዊነቱም የአምባሳደሩ የማይነጥፍ ድጋፍ የጎላ ድርሻ እንዳለው አብራርቷል።
አምባሳደሩ ከወረዳው ከዞኑም አልፎ በተለያዩ አካባቢዎች በተለይም በትምህርት ዘርፍ ላይ ኢንቨስት በማድረግ ለትውልድ የሚተላለፍ አሻራቸውን በማኖር ላይ የሚገኙ የልማት አርበኛ እንደሆኑም ጠቁመዋል።
የህብረተሰቡን ችግር የኔም ችግር ነው በማለት የመፍትሔ አካል በመሆን እያኖሩት ላለው ዘመን ተሻጋሪ ልማት አቶ መብራቱ በራሳቸውና በወረዳው ህዝብ ስም ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል።
የትምህርት ጥራትና የተማሪ ውጤት ለማሻሻል እየተደረገ ባለው ጥረት የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን የጠቆሙት ዋና አስተዳዳሪው በተለይም ወላጆች ልጆቻቸውን ውጤት እንዲያስመዘግቡ መምከርና መከታተል ይኖርባቸዋል ብለዋል።
የወረዳው የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ሞሸዲን አህመድ እንደገለጹት የተማረ ትውልድ ማፍራት የውዴታ ግዴታ በሆነበት በአሁኑ ወቅት የአምባሳደሩ ድጋፍ ከፍተኛ ምስጋና የሚገባው ነው።
በትምህርት ላይ ኢንቨስት የሚያደርጉት አርቆ አስተዋዮች ናቸው ያሉት አቶ ሞሸዲን በአምባሳደር ምስጋኑ አርጋ አማካኝነት የተገኘውን እድል በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል።
ልጆች ወደ ትምህርት ቤት መላክ ብቻውን ግብ እንዳልሆነ የጠቀሱት የወረዳው የመንግስት ዋና ተጠሪ ውጤት አስመዝግበው ሀገር አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ማብቃት ወሳኝ ጉዳይ ነው ብለዋል።
እንደ አካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ ትምህርት ወላጆች ለልጆቻቸው የሚያስተላልፉት ውርስ በመሆኑ በውጤት እንዲታጀብ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማበርከት እንዳለባቸውም አቶ ሞሸዲን አስረድተዋል።
የወረዳው ትምህርት ጽ/ቤት ምክትል ሐላፊ አቶ በሳአቱ ብርጉ በወረዳው ተግባራዊ እየተደረገ በሚገኘው ትምህርት ለትውልድ ፕሮግራም የትምህርት ቤቶች ደረጃና የተማሪ ውጤት ለማሻሻል የሚያስችሉ በርካታ አበረታች ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ጠቁመው አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ትልቁን ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝ ጠቁመው ምስጋና አቅርበዋል።
የሸብራበር 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ሹአይብ ናስር በበኩላቸው አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ እያደረጉት ያለው ድጋፍ ተዘርዝሮ የማያልቅ መሆኑን ጠቁመው ልባዊ ምስጋና አቅርበዋል።
በዕለቱም ከ4ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ወጪ በማድረግ 1ሺ 3መቶ ለሚሆኑ ለት/ቤቱ ተማሪዎች በሙሉ ዩኒፎርምና የመምህራን ገዋን ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
የ12ኛ ክፍል ተማሪ ኢብራሂም ረሻድ እና የ10ኛ ክፍል ተማሪ ኤደን መሰረት በጋራ በሰጡት አስተያየት የወረዳው መንግስትና አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በትምህርት ላይ እያደረጉት ላለው ድጋፍና ክትትል ምስጋናቸውን አቅርበው ውጤት በማስመዝገብ ውለታ ከፋይ ለመሆን መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል።
በፕሮግራሙ ላይ የወረዳው የመንግስት ረዳት ተጠሪ አቶ አበበ አገዘ፣የአምባሳደሩ ስራ ባልደረቦች ፣የት/ቤቱ መምህራን የተማሪ ወላጆችና ተማሪዎች ተገኝተዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *