“የጉራጌ ቡና” ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብና ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጲያ ክልል ቡናና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ቢሮ ገለፀ።

ታህሳስ 16/2018 ዓ.ም
================
“የጉራጌ ቡና” ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብና ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጲያ ክልል ቡናና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ቢሮ ገለፀ።
ከማዕከላዊ ኢትዮጲያ ክልል የተወጣጣ ቡድን በእኖር ወረዳ የቡና ምርት፣
ዝግጅትና ጥራት አጠባበቅ ላይ በአርሶአደሩ ጓሮ የመስክ ጉብኝት አድርጓል።
በጉብኝቱ ላይ የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጲያ ክልል ቡናና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ምክ/ዋና ዳይሬክተርና የምርት ዝግጅትና ገበያ ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሳምሶን ወ/ጊዮርጊስ እንደገለጹት ጉብኝቱ የቡና ምርት ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ የሚደረገው ተግባር ማጠናከርን ያለመ መሆኑንም አመላክተዋል።
በመሆኑም ቡና በጥራት አምርቶ አርሶአደሩና መንግስት በዘርፉ ተገቢውን ጥቅም እንዲያገኙ ከችግኝ ዝግጅት ጀምሮ ልዩ ጥበቃና እንክብካቤ ማድረግ እንደሚገባም አመላክተዋል።
ኃላፊው በወረዳው በዘርፉ የተሻለ ምርት ለማግኘት የባለሙያና የአርሶአደሩ ቅንጅታዊ ስራ አበረታች መሆኑንም ጠቁመዋል።
በጉራጌ ዞን ግብርና መምሪያ የቡናና ቅመማ ቅመም ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ቢረዳ እንዳሉት በዞኑ እምቅ የቡና ምርት ጸጋ በመኖሩ አርሶአደሩ ተጠቃሚ እየሆነ ይገኛል።
በዞኑ ቡና የሚመረትባቸው ወረዳዎች በስፋት እንዲመረት በማድረግና በሀገሪቱ ከፍተኛ ጣእም ያለው “የጉራጌ ቡና” ብራንድነቱን ተጠብቆ እንዲሄድ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በዚህ ዘርፍ ባለሀብቱ ያሳተፈ ስራ እንደሚሰራ ያመላከቱት ኃላፊው አርሶአደሩና ሀገር በዘርፉ ተገቢውን ጥቅም እንዲያገኝ ከወረዳዎች ህገ ወጥ የቡና ተቆጣጣሪ ግብረ ሀይሎች ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት ምክትል ሐላፊና የቡና ልማት ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ሙሉጌታ ሟነንጋ በወረዳው እየተመረተ ያለውን ቡና ለአለም ገበያ እንዲቀርብ በፌዴራል ደረጃ የብራንድ እውቅና ማግኘቱን ጠቁመው ለዚህም አስፈላጊውን ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።
በመሆኑም በወረዳው በ2018 ዓ.ም 45 ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በወረዳው የቡና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግና የአርሶ አደሩን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማሻሻል እየተደረገ ባለው ጥረት ሁሉም የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲያበረክት አቶ ሙሉጌታ መልዕክት አስተላልፏል።
ቡድኑ በመጨረሻም በወረዳው ጉስባጃይ ከተማ (በFSRP) ፕሮግራም አየተገነባ ያለው የቡና ምርት ማከማቻና መሸጫ መጋዘን ያለበትን ደረጃ ጎብኝቷል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *