ለዜጎች ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠትና ዲጂታል ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ ህብረተሰቡ የፋይዳ መታወቂያ ባለቤት መሆን እንዳለበት ተገለጸ

ለዜጎች ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠትና ዲጂታል ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ ህብረተሰቡ የፋይዳ መታወቂያ ባለቤት መሆን እንዳለበት ተገለጸ።
በእኖር ወረዳ “ዲጂታል ኢትዮጵያን ዕውን ማድረግ ለሁለንተናዊ ብልጽግና”በሚል መሪ ሃሳብ የ2017 ዓ.ም የፋይዳ መታወቂያ ምዝገባ አፈጻጸምና የ2018 ዓ.ም የምዝገባ ፍቃድ ዝግጅት የተመለከተ የንቅናቄ መድረክ በጉንችሬ ከተማ ተካሒዷል።
መድረኩን የመሩት የእኖር ወረዳ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ሐላፊ አቶ ፍቅሬ መልስ እንዳሉት የፋይዳ መታወቂያ ዋና አላማ ለዜጎች ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠትና ዲጂታል ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ ያለመ መሆኑን ጠቁሟል።
በመሆኑም እድሜያቸው ከ5 ዓመት በላይ የሆኑ የህብረተሰቡ ክፍሎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በየቀበሌው በሚደረገው የፋይዳ መታወቂያ ምዝገባ ፕሮግራም ላይ በንቃት እንዲሳተፉ አቶ ፍቅሬ አሳስቧል።
ባለፈው አመት ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ከመፍጠር፣የሰለጠነ የሰው ሃይል ከማሰማራት፣ከመገልገያ ቁሳቁስ (ኪት)
ውስንነት፣ከመረጃ ልውውጥ፣ከመብራት መቆራረጥና ከኔትዎርክ ጋር ተያይዞ ክፍተት መስተዋሉን አስታውሷል።
ያጋጠሙ ችግሮች በተቻለ መጠን ለማስተካከል ጥረት ይደረጋል ያሉት ሐላፊው ተናቦና ተቀናጅቶ በመስራት ህብረተሰባችን የፋይዳ መታወቂያ ሁለንተናዊ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን መትጋት ያስፈልጋል ብሏል አቶ ፍቅሬ።
የወረዳው አስተዳደር ጽ/ቤት የመሰረተ ልማት ዘርፍ ሐላፊ አቶ አድርሴ ተረዳ አጭር የንቅናቄ ሰነድ አዘጋጅተው በማቅረብ ማብራሪያ ሰጥቷል።
በበጀት አመቱ በኢትዮ ቴሌ እና በኢትዮ ፖስታ አማካኝነት በወረዳው ከ60 ሺ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች የዲጂታል ፋይዳ መታወቂያ ባለቤት ለማድረግ መታቀዱንም አቶ አድርሴ ገልጿል።
የተለያዩ የሚዲያ አማራጮችና የስብሰባ መድረኮችን በመጠቀም ለህብረተሰቡ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ እንደሆነም አመላክቷል።
በውይይቱ ላይ የሚመለከታቸው የአቢይ እና የቴክኒክ ኮሚቴ አባላት የተገኙ ሲሆን ተሳታፊዎቹ እንዳሉት ዲጂታል ፋይዳ መታወቂያ ምዝገባ አንዱ የልማት ዕቅድ አካል እንደሆነ ጠቁመው ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሰጥተው ለህዝብ ተጠቃሚነት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
በቀጣይ ተግባር ወቅት ሊገጥሙ በሚችሉ ተግዳሮቶችና መፍትሔዎቹ ዙሪያ ሀሳብ በመለዋወጥ ተቀናጅቶ ወደ ስራ ሊያስገባ የሚያስችል መልካም ተግባቦት የተፈጠረበት መድረክ እንደሆነም ገልጸዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *