በ2017 ዓ/ ም የበጋ የመስኖ ተግባር ከ2 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የተገኘውን የውሃ አማራጮች በመጠቀም የተለያዩ የአትክልት ምርቶችን ማምረት መቻሉን በጉራጌ ዞን የእኖር ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ገለፀ ።
በማህበር ተደራጅተው በበጋ መስኖ በማምረት የገቢ አቅማቸው ማሳደግ መቻላቸውን በወረዳው አጋሬ ቀበሌ ቃንዠ በር ማህበር አባላት ተናግረዋል፡፡
የእኖር ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ አብድል መጂድ ጀማል በግብርናው ዘርፍ በአመት አንድ ጊዜ ብቻ ከማምረት ልምድ በመውጣት ሁለቴና ከዚያ በላይ አርሶ አደሩ ማምረት እንዲችል የተለያዩ ጥረቶች እየተደረገ ይገኛል ብለዋል ።
በ2017 የበጋ መስኖ ስራም 2 ሺ 2 መቶ ሄክታር መሬት ለማምረት ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን የተናገሩት ሀላፊው በእስካሁኑ ሂደትም 2ሺ 1 መቶ ሄክታር መሬት የተገኘውን የውሀ አማራጮች በመጠቀም የተለያዩ የአትክልት ምረቶችን ማምረት መቻሉን ተናግረዋል።
ምርታማነትን ማሳደግ እንዲቻል ከሌሎች ባለድርሻ አከላት ጋር በመቀናጀት አስፈላጊውን ግብአት በወቅቱ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ መደረጉንም አስታውሰዋል አቶ አብድልመጂድ።
በቀጣይም የተመረተው ምርት አርሶ አደሩ በተመጣጣኝ ዋጋ ገበያ ማቅረብ እንዲችል ትራንስፓርት መመቻቸቱንና የገበያ ትስስር መፍጠር ተግባርም እንደሚከናወን ሀላፊው እስረድተዋል ።
በወረዳው የአጋሬ ቀበሌ የግብርና ባለሙያ አቶ ደሳለኝ መልካሙ በቀበሌው የተለያዩ አደረጃጀቶችን በመጠቀም ብሎም የቀበሌው አርሶ አደር በየጓሮው የሚያገኘውን የውሀ አማራጮችን ተጠቅሞ በበጋ መስኖ አትክልቶችን በማምረት የገቢ አቅሙን ማሳደግ እንዲችል ሙያዊ ድጋፋቸውን እየሰጡ መሆኑን አስረድተው አሁን ላይ የተዘራው የሽንኩርት ዘርም ለገበያ ማቅረብ ደረጃ መድረሱንም ተናግረዋል።
በወረዳው አጋሬ ቀበሌ አግኝተን ያነጋገርናቸው የቃንዠበር የበጋ መስኖ ተግባር ማህበር አባል መካከል አቶ ሰፋ ኬርሳዊና አብረሀም ወልዴ በማህበር ተደራጅተው ወደ መስኖ ተግባር ከገቡ ብዙ ጌዜ እንዳስቆጠሩና ባመረቱት ምርትም ከጊዜ ወደ ጊዜም የገቢ አቅማቸውን ማሳደግ መቻላቸውን ገልፀዋል።
በተያዘው የምርት ዘመንም የናካብ የወንዝ ውሃን በመጠቀም የሽንኩር ምርት ማምረት ችለናል ብለዋል።
አሁን ላይ ምርቱ ወረዳው በሚያዘጋጅላቸው ትራንስፓርት ተጠቅመው ለገበያ እንደሚያቀርቡ ተናግረው ለምርታማነቱ የሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ድጋፍና ክትትል እንዳልተለያቸውም አብራርተዋል።




