የካቲት 3/2017 ዓ.ም
==============ብቁ እና ተወዳዳሪ ዜጋ ለማፍራት ሀገር በቀል ዕዉቀቶችን በሳይንስና ቴክኖሎጂ በማስደገፍ ለላቀ አገልግሎት እንዲበቁ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ ተገለፀ።
በእኖር ወረዳ ሳ/ኢ/ቴ/ጽ/ቤት አዘጋጅነት በኢትዮ ኮደርስ፣በሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራ ስራዎች፣ እንዲሁም በኢኮቲ ማቴሪያል ቅድመ ብልሽት ላይ ያተኮረ ለሁሉም የሳይንስና ቴክኖሎጂ ክበብ ተጠሪ መምህራን እና ለሱፐርቫይዘሮች ሲሰጥ የነበረው የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ተጠናቀቀ።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የወረዳው ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ዲንሰፋ ጀማል በዚህ ወቅት እንዳሉት ብቁ እና ተወዳዳሪ ዜጋ ለማፍራት ሀገር በቀል ዕዉቀቶችን በሳይንስና ቴክኖሎጂ በማስደገፍ ለላቀ አገልግሎት እንዲበቁ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
ያደጉ ሀገራት የዕድገታቸው ትልቁ ሚስጥር ለሳይንስና ቴክኖሎጂ በሰጡት ልዩ ትኩረት መሆኑንም አውስተዋል።
ዘመኑ የቴክኖሎጂ እንደመሆኑ መጠን በወረዳው በሁሉም ደረጃ ብቁ እና ተወዳዳሪ ዜጋ ለማፍራት በሚደረገው ጥረት ሁሉም በቅንጅት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
ሀላፊው አክለውም ዘርፉን የማህበረሰቡን ችግር ለመፍታትና ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጥ እይታ ላይ ያተኩራል ነው ያሉት።
ኢትዮ ኮደርስ ወጣቱ ትውልድ ዲጂታል በሆነው አለም ውስጥ በመሳተፍ የስራ ዕድል የሚፈጥር ትልቅ ዕድል ነው ሲሉ አስገንዝበዋል።
ይህ የኢትዮ ኮደርስ ኢኒሼቲቭ ሁሉንም ለማብቃት ታልሞ የተጀመረ መሆኑን ያብራሩት አቶ ዲንሰፋ ለመጪው ትውልድ ጭምር ለማሸጋገር መስራት እንደሚጠበቅብን መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የጉራጌ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ የፈጠራ ስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ታሪኩ ነዳ እንደገለፁት በየደረጃው የሚገኙ የፈጠራ ስራዎችን ፈልቀዉ፣ለምተው እና ተሸጋግረው በሀገር ልማት ላይ አዎንታዊ ለውጥ እንዲያመጡ ይሰራል ብለዋል።
የፈጠራ ውጤቶችን የኢኮኖሚ ብዝሀነትን ያሳድጋሉ ያሉት አስተባባሪው ቴክኖሎጂ የችግሮቻችን ሁሉ መፍትሔ መሆኑን በንግግራቸው ጠቁመዋል።
እንደ አቶ ታሪኩ ገለፃ ሀገራችን ከሌሎች ሀገራት እኩል ለመሰለፍ ትምህርት ቤቶች ላይ ክበባት በማጠናከር ዘርፉን በተገቢው መጠቀም እንደሚያስፈልግም አንስተዋል።
ስለሆነም የህዝብ አኗኗር የሚቀየረው እና ልማት የሚያድገው በፈጠራና ምርምር ስራዎች በመሆኑ ሰልጣኞች ያገኙትን ስልጠና ወደ ተግባር መቀየር እንዳለባቸው አጽንዖት ሰጥተዋል።
ከተሳታፊዎች መካከል አንዳንዶቹ በሰጡት አስተያየት ስልጠናው አስተማሪና ለቀጣይ ተግባር የሚያነሳሳ መሆኑን ጠቁመው የኢትዮ ኮደርስ ኢኒሼቲቭ በመቀላቀል በፈጠራ የታጀበ ፍጥነት ለመከተል መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
በመድረኩ ማጠቃለያ ከሸብራበር 2ኛ ደረጃ ት/ቤት በተማሪ እሱባለው ተክለወልድ የተሰራ”እስማርት አግሪ ካልቸር ሲስተም”በሰልጣኞች ተጎብኝቷል።
በስልጠናው የእኖር ወረዳ ም/ል አስተዳዳሪና የትምህርት ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ሽኩረታ አ/ከሪም፣የወረዳው ሳ/ኢ/ቴ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ዲንሰፋ ጀማል፣የጉራጌ ዞን ሳ/ኢ/ቴ/መምሪያ የፈጠራ ስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ታሪኩ ነዳን ጨምሮ፣የወረዳው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ከበብ ተጠሪ መምህራን፣ ሱፐርቫይዘሮች እና ሌሎችም መሳተፋቸውን የወ/መ/ኮ ዘግቧል።




