የካቲት 1/2017ዓ.ም
=============
የእኖር ወረዳ መምህራን ማህበር ምክር ቤት 28ኛ መደበኛ ጉባኤ በጉንችሬ ከተማ ተካሔደ።
ምክር ቤቱ ባካሔደው 28ኛ መደበኛ ጉባኤ መምህር አዲሱ በሰኔ የወረዳው መምህራን ማህበር ሊቀመንበር እንዲሁም መምህርት በላይነሽ ዘፕሬ የማህበሩ ጸሐፊ አድርጎ ሾመ።
በጉባኤው ላይ የተገኙት የወረዳው ምክትል አስተዳዳሪና የትምህርት ጽ/ቤት ሐላፊ አቶ ሽኩረታ አብድልከሪም እንደተናገሩት መምህርነት እጅግ ተወዳጅና ትውልድ የሚቀረጽበት ሙያ መሆኑን ጠቁሟል።
በመሆኑም መምህራን ይህንኑ ክቡርና ውድ ሙያቸውን ተጠቅመው የትምህርት ጥራትና የተማሪ ውጤት በማሻሻል በትውልድ ላይ ዘመን ተሻጋሪ ታሪክ እንዲሰሩ በምክር ቤቱ አባላት በኩል ለወረዳው መምህራን ጥሪ አስተላልፏል።
የወረዳው መንግስት አቅም በፈቀደ መጠን ከምንም ነገር በላይ የመምህራን መብት በመጠበቅ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝም አብራርቷል።
በትምህርት ዘርፍ እየገጠመ ያለው የጥራትና የውጤት ስብራት ለመጠገን እየተሰራ ባለው ስራ መምህራን የአንበሳውን ድርሻ እንደሚወስዱም አስረድቷል።
ከጡረታ መለያ ቁጥር፣ እንዲሁም ከመምህራን እጥረትና ከመሳሰሉት ጋር ተያይዞ በጉባኤው የቀረቡ ክፍተቶች ለማስተካከል ጥረት እንደሚደረግም አቶ ሽኩረታ ጠቁሟል።
የወረዳው መምህራን ማህበር የ 8 ወር አፈጻጸም ሪፖርት በማህበሩ ሰብሳቢ በአቶ ተክሉ ማቲያስ ቀርቦ አባላቱ የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶችን በማንሳት መክረውበታል።
ለተነሱ ጥያቄዎች በሰብሳቢው እና በሚመለከታቸው አመራሮች በኩል ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቿል።
በምክር ቤቱ የተገኙት የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ መብራቴ ተክሌ በሰጡት አስተያየት በወረዳው በአመት ከ80 ሚሊየን ብር በላይ ለመምህራን ደመወዝ እንደሚከፈል ጠቅሷል።
በወረዳው የትምህርት ጥራት መሰረት እንዲኖረው ከታች ከ”ኦ” ክፍል ጀምሮ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝም አመላክቷል።
የተማሪ ውጤት ማሻሻል እንቅልፍ የሚሰጥ ጉዳይ እንዳልሆነ የጠቆሙት ዋና አስተዳዳሪው በትምህርት ልማት ላይ በንቃት እየተሳተፈ የሚገኘው የወረዳው ህዝብ በትምህርት ላይ ተስፋ እንዳይቆርጥ በተለይም መምህራንና ተማሪዎች አቅማቸውን አሟጠው እንዲጠቀሙ አደራ ብሏል።
በጉባኤው ላይ የተገኙት የጉራጌ ዞን መምህራን ማህበር ሊቀመንበር አቶ ደጀኔ እስጢፋኖስ ወረዳው ለትምህርት ውጤታማነትና ለመምህራን እየሰጠው ላለው ክብርና እያደረገ ለሚገኘው ሁለንተናዊ ድጋፍ ከፍተኛ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በተመሳሳይ መልኩ ለወረዳው መምህራን ማህበር መጠናከር የወረዳው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑንም አመላክቷል።
ምክር ቤቱ የመምህራን ማህበር ተወካይ የምርጫ ዘመን መጠናቀቁን ተከትሎ ለቀጣይ አራት አመታት የወረዳው መ/ማህበር የሚመሩ አምስት ስራ አስፈጻሚ በመምረጥ ቃለ መሃላ አስፈጽሟል።
በጉባኤው ማጠቃለያ ላይ በቀጣይ በተማሪ ውጤትና ስነ ምግባር ላይ ተጨባጭ ለውጥ ለማስመዝገብ፣የመምህራን መብትና ጥቅማጥቅም ለማስከበርና ግዴታንም በተገቢው ለመወጣት ያለመ ባለ አምስት ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት በመምህር በላቸው ተክሌ ቀርቧል።
በመጨረሻም ከ25 አመት በላይ በመምህርነት ያገለገሉ መምህራን፣ጡረታ የወጡ መምህራን፣ የቀድሞ የወረዳ መ/ማህበር ስራ አስፈጻሚዎች በወረዳው አስተዳደርና ትምህርት ጽ/ቤት በኩል የተዘጋጀላቸውን የአልባሳት፣የገንዘብና የምስጋና ምስክር ወረቀት ተበርክቶላቿል።
ለወረዳው አስተዳደር፣ለትምህርት ጽ/ቤት እና ለፋይናንስ ጽ/ቤት የወረዳው መምህራን ማህበር ለማጠናከር እያደረጉት ላለው ድጋፍ በማህበሩ በኩል ማበረታቻና ከፍተኛ ምስጋና ተችሯቸዋል። ዘገባው የወረዳው መ/ኮ ነው።







