ግብርናውን ከዝናብ ጥገኝነት ለማላቀቅ በመስኖ አማራጮች አጠቃቀም ላይ የዘርፉ ባለሙያዎች አቅም ማሳደግ እንደሚገባ ተገለፀ።
የስርዓተ-ምግብ ማሻሻያና ማጠናከሪያ(FSRP)ፕሮግራም ወቅታዊ የግብርና መስኖ ሰብሎች አግሮኖሚ(የውሀ አጠቃቀም)በሽታና ተባይ ቁጥጥር፣ እንደዚሁም የቦካሽ የተፈጥሮ ማዳበርያ አዘገጃጀት ዙርያ ለግብርና ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና ሰጥቷል።
የFSRP ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ጌቱ ኮራ ስልጠናው በሰጡበት ወቅት ላይ እንደገለፁት ፕሮግራሙ ግብርናውን በማዘመን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ፣የእንስሳትና አሳ ሀብት ለማሻሻል፣አነስተኛ የመስኖ ውሃ ተቋማት ለማጠናከርና ለማስተዳደር ፣ለወጣቶች የስራ-ዕድል ለመፍጠር፣የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና ሌሎችም በርካታ ተግባራት ላይ አላማ አድርጎ እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
አክለውም በመስኖ ውሃ አጠቃቀም እና ያሉት ትሩፍቶች፣በመስኖ ለማልማት እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶች፣በመስኖ አጠቃቀምና ምርት ወቅት የሚያጋጥሙን ችግሮች መፍትሔዎቻቸው እንደዚሁም በሰው ሰራሽ ማዳበርያ አዘገጃጀት ዙርያ የዕለቱ የስልጠናው ዋና ዋና ተግባራቶች ናቸው።
እንደ አቶ ጌቱ ገለፃ የመስኖ ልማት ከየትኛውም የግብርና ልማት ስራዎች ቴክኖሎጂ በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ የሚያስችልና በአጭር ጊዜ ውስጥ ትርፋማ የሚያደርግ ዘርፍ መሆኑንም አብራርተዋል።
ለዚህም እንደ ሀገር ያለንን መልማት የሚችል መሬት አቅም በአግባቡ ለመጠቀም የውሃ አማራጮችን መሠረት ያደረገ የመስኖ ልማት ስራን ማስፋፋት ያስፈልጋል ብለዋል።
የቴክኖሎጂ እጥረት፣የበሽታዎች ክስተትና የብድር አገልግሎት በመስኖ ለማምረት እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶች መሆናቸውን ጠቅሰው ተከታታይ የሆነ የበሽታ ክትትል ማድረግ፣ የቴክኖሎጂና የብድር አቅርቦት ማስፋት የሚያጋጥሙ ችግሮች መፍትሔ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ አ/መጅድ ጀማል በዚህ ወቅት እንዳሉት መደበኛ የመስኖ ልማት ተግባር ለምግብ ዋስትናችን ሰፊ ድርሻ ያለው በመሆኑ በክህሎት የበለፀገ የባለሙያ ዝግጅት በማስፈለጉ ስልጠናው መዘጋጀቱን አብራርተዋል።
የስልጠናው ድምር ውጤት የተፈጥሮ ጸጋዎችን ወደ ልማት በመቀየር ድህነትን ታሪክ ለማድረግ እንዲሁም ከድህነት የተሻገረ ቤተሰብ፣ማህበረሰብና ሀገርን እዉን ማድረግ መሆኑን ሀላፊው አመላክተዋል።
ግብርናውን ከዝናብ ጥገኝነት ለማላቀቅ በመስኖ አማራጮች አጠቃቀም ላይ የዘርፉ ባለሙያዎች አቅም ማሳደግ ይገባልም ነው ያሉት።
ሀላፊው አክለውም የግብርናው ዘርፍ ከድህነት መውጫ ዋነኛ መንገድ ነው ያሉ ሲሆን ከኋላ ቀር የግብርና አሰራርና ከዝናብ ጠባቂነት በመላቀቅ በአመት ሁለትና ሶስት ጊዜ በማምረት በቤተሰብ፣በማህበረሰብና በሀገር አቀፍ ደረጃ ድህነትን ለማሸነፍ እየተካሄደ ያለው ጥረት ስኬታማ ለማድረግ የሁሉም አካላት ርብርብ እንደሚጠይቅም አንስተዋል።
ወቅቱ የደረሱ ሰብሎችን የሚሰበሰቡበት እንደመሆኑ መጠን በተደራጀና በተቀናጀ መንገድ ሰብሎችን መሰብሰብና የምርት ብክነትን ማሻሻል እንደሚገባም አቶ አ/መጅድ አሳስበዋል።
የጽ/ቤቱ ምክትልና የእርሻ ዘርፍ ሀላፊ አቶ መስፍን ወንድሙ በበኩላቸው ባለሙያዎች በየጊዜው የሚያገኙትን ስልጠና ወደ ተግባር ለመቀየር ተቀናጅቶ መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የስልጠናው ሰነድ በዘርፉ ባለሙያዎች የቀረበ ሲሆን ይህም በአትክልት ሰብሎች አግሮኖሚ(በጥቅል ጎመን፣በቲማቲምና በቀይ ሽንኩርት አመራረት)፣በሰብል ጥበቃው ዘርፍ(በዋና ዋና አዝርዕት ሰብሎች ተባዮች፣የበሽታዎች ስነ-ባህሪይ እና የመከላከያ ዘዴዎች) ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልፀዋል።
ከስልጠናው ጎን ለጎን በሰው ሰራሽ ማዳበርያ(ቦካሽ የተባለ አዲስ ቴክኖሎጂ)አዘገጃጀት ዙርያ የተግባር ስልጠና ተሰጥቷል።
ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል አንዳንዶቹ በሰጡት አስተያየት ስልጠናው ወቅቱን የጠበቀና የነበረባቸውን ጉድለት በመቅረፍ ከአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ጋር መተዋወቅ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።
