በእኖር ወረዳ የትምህርት ቤቶች ደረጃ፣የተማሪዎች ውጤትና ስነ ምግባር ለማሻሻል የተጀመረውን የትምህርት ልማት ስራ በላቀ ሁኔታ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የወረዳው አስተዳደር ገለጸ።
የወረዳው ትምህርት ጽ/ቤት”የላቀ ትጋት ለትምህርት ጥራት”በሚል መሪ ቃል የ2017ዓ.ም የትምህርት ጉባኤ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በጉንችሬ ከተማ አካሂዷል።
የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ መብራቴ ተክሌ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ትምህርት የእድገትና ብልፅግና ቁልፍ መሳሪያ በመሆኑ ስራው በጥራትና ሁለንተናዊ ተሳትፎ በማሳደግ ተግባራዊ ማድረግ ይገባል።
በመሆኑም በወረዳው የትምህርት ቤቶች ደረጃ፣የተማሪዎች ውጤትና ስነ ምግባር ለማሻሻል የተጀመረውን የትምህርት ልማት ስራ በላቀ ሁኔታ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ዋና አስተዳዳሪው ገልጸዋል።
ባለፈው አመት የወረዳው ህብረተሰብ በማስተባበር ከ 120 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የትምህርት ልማት ስራ መከናወኑን አስታውሰዋል።
መሪነት በተግባር የሚገለጽ በመሆኑ በትምህርት ስራው ላይ የሚፈለገውን ጥራትና ውጤት ለማስመዝገብ የሞት ሽረት ትግል ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
ለዚህም የአመራሮች፣የመምህራን፣የተማሪዎች፣የወላጆችና የሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ ተቀራርቦና ተቀናጅቶ መስራት እንደሚገባም ተናግረዋል።
ላለንበት የቴክኖሎጂው አለም የሚመጥን ብቁና ተወዳዳሪ ትውልድ ለማፍራት ሁሉም በቁጭትና በጊዜ የለንም መንፈስ ከወዲሁ ወደ ተግባር መግባት ይኖርብናል ብለዋል።
የወረዳው ምክትል አስተዳዳሪና የትምህርት ጽ/ቤት ሐላፊ አቶ ሽኩረታ አብድልከሪም የወረዳው የ2016ዓ.ም አጠቃላይ የትምህርት ስራ አፈጻጸምና የ2017 ዓ.ም ዕቅድ ክንውን እንዲሁም በወልቂጤ ዩንቨርስቲ የተጠና የ12ኛ ክፍል ውጤት ተግዳሮት ሰነድ በማቅረብ ለተሳታፊዎች አብራርቷል።
የትምህርት ጥራት ችግር ሀገር አቀፍ ውድቀት በመሆኑ ከላይ የተቀመጠውን አሰራር በመከተል በወረዳው አምና በተካሔደው “ትምህርት ለትውልድ”ንቅናቄ ፕሮግራም በትምህርት ላይ እጅግ የሚያስመሰግን ስራ መሰራቱን ተናግሯል።
በወረዳው መንግስትና በህብረተሰቡ ተሳትፎ ከ 9 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የመማሪያ መጽሐፍት ግዢ በመፈጸምና እጥረቱን በማሻሻል ለዞን ተሞክሮ የሚሆን ተግባር መከናወኑንም ጠቁሟል።
የወረዳው ህብረተሰብ ለትምህርት ሲባል ጉልበቱን ሳይቆጥብና ገንዘቡን ሳያሳዝነው በንቃት እየተሳተፈ የሚገኝ ባለውለታ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሽኩረታ የተማሪዎች ውጤት በማሻሻል ውለታውን መካስ እንደሚገባም አስገንዝቧል።
ወረዳው በ6ኛ እና በ8ኛ ክፍል ውጤት በዞኑ ስር ካሉ አቻ ወረዳዎች የተሻለ ቢሆንም 12ኛ ክፍል ላይ ያጋጠመው የውጤት ማጣት ችግር በዘላቂነት ለማሻሻል ከታች ከቅድመ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት ጀምሮ ለመስራት ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን አመላክቷል።
የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ወስደው ከነበሩ ተማሪዎች መካከል በቁጥር 37 የሚሆኑት በሪሚዲያል ወደ ዩኒቨርስቲ መግባታቸውንም ጠቁሟል።
በአሁኑ ወቅት በወረዳው ውስጥ በሚገኙ በ45 አንደኛ ደረጃ እና በ7 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በአጠቃላይ ከ 20 ሺ በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ እንደሚገኙም ሐላፊው ገልጿል።
የቅድመ መደበኛ ትምህርት ጣቢያዎች ደረጃ ማሻሻልና መለወጥ የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ ወሳኝ መፍትሔ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ ሽኩረታ የትውልድ አደራና ሐላፊነት በአግባቡ መወጣት ይገባልም ብለዋል።
የወረዳው የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ሞሸዲን አህመድ በበኩላቸው በትምህርት ስራ ላይ ውጤት ለማስመዝገብ የተማሪዎች ትጋትና ተነሳሽነት በማሳደግ የወላጆችና የመምህራን ድጋፍና ክትትል ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል።
ተግባሩንም ከአመራሩ ጀምሮ በቁርጠኝነት በመያዝና በመገምግሞ ፈጣን መፍትሔ አስቀምጦ መምራት ይጠይቃል ብለዋል።
የወረዳው ህዝብና አጋር ድርጅቶች በማስተባበር የትምህርት ግብአት እጥረት ለማሟላት ከወዲሁ የንቅናቄ ስራዎችን መጠናከር እንዳለባቸውም ጠቅሷል።
የጉራጌ ዞን የፋይናንስ መምሪያ ሐላፊ /የወረዳው ደጋፊ አመራር አቶ አብዶ ሀሰን በሰጡት ማጠቃለያ ሀሳብ የትምህርት ጥራትና ውጤት በአንድ ጀንበር የሚመጣ እንዳልሆነ ጠቁመው በወረዳው መንግስትና በህብረተሰቡ ተሳትፎ እየተደረገ ያለው ጥረት ተስፋ ሰጪ መሆኑን ገልጸዋል።
በትምህርት ላይ የአመለካከት ለውጥ በማምጣት፣ከቅድመ 1ኛ ደረጃ ጀምሮ የት/ቤቶች ደረጃ በማሻሻል፣የተጀመረውን የጉራጊኛ ቋንቋ ትምህርት በማጠናከር ፣የተማሪ ውጤትና ስነ ምግባር ማሻሻል እንደሚገባም አብራርቷል።
አንዳንድ የጉባኤው ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት በትምህርት ስራው ላይ ያጋጠሙ ችግሮች በመፍታት የቁጥጥርና የክትትል ስርአቱን በማጠናከርና የህብረተሰቡን ተሳትፎ በማሳደግ ትውልድ የመቅረጽ አደራቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።
በመጨረሻም በ2016 ዓ.ም የተሻለ አፈጻጸም ለነበራቸው አካላት ምስጋና/ዕውቅና በመስጠትና የ2017 ዓ.ም የትምህርት ግብ ስምምነት በመፈራረም ጉባኤው ተጠናቋል



