በጉራጌ ዞን እኖር ወረዳ በ70 ሚሊየን ብር የተገነባው የካናስ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ።

ሀምሌ 27/2016 ዓ.ም
በጉራጌ ዞን እኖር ወረዳ በ70 ሚሊየን ብር የተገነባው የካናስ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ።
በዞኑ በህዝብና በመንግስት የጋራ ቅንጅት በተሰሩ ተግባራት የህብረተሰቡ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ መፍታት እየተቻለ መሆኑን የጉራጌ ዞን አስተዳደር አስታወቀ።
የካናስ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ከተጀመረ 8 አመታት ያስቆጠረ ሲሆን ዛሬ ተመርቆ አገልግሎት በመስጠቱ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።
የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ በዞኑ በማህበረቡና በመንግስት ትብብር በርካታ የልማት ስራዎች ተሰርቷል ያሉ ሲሆን በእኖር ወረዳም በመንገድ፣በትምህርትና በመሰል ተግባራት እየተሰሩ ያሉ ግንባር ቀደም ስራዎች አጠናክሮ ማስቀጠል ያስፈልጋል ብለዋል።
በዞኑ በህዝብና በመንግስት የጋራ ቅንጅት በተሰሩ ተግባራት የህብረተሰቡ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ መፍታት እየተቻለ መሆኑን አመላክተዋል።
አቶ አበራ ውሃውን ክትትል በማድረግ በዘላቂነት ለትውልድ እንዲተላለፍ መስራት እንደሚገባ መክረው የዞኑ መንግስትም በሚሰሩ ስራዎች ድጋፋን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግሯል።
የጉራጌ ዞን ውሃና ማእድን ኤነርጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ አየለ ፈቀደ በበኩላቸው ዞኑ በርካታ የገጸ ምድርና የከርሰ ምድር ውሃ ያለው ሲሆን መንግስት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣የልማትና ባህል ማህበር፣ባለሀብቶች እና ማህበረሰቡ በማሳተፍ የህብረተሰቡ የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር ለመቅረፍ እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።
የእኖር ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መብራቴ ተክሌ የካናስ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት በወርልድ ቪዥን ድርጅት ሲሰራ የቆየ ሲሆን ድርጅቱ በ2015 ዓ.ም ከወረዳው በመውጣቱ የተነሳ ከዚያ በኋላ ግን የወረዳው መንግስት ተቀብሎ ከህብረተሰቡ ጋር በጋራ ሲሰራው እንደነበር አስገንዝበዋል።
በአካባቢው ለዘመናት የንጹህ መጠጥ ውሃ ባለመኖሩ በጤና እክል ላይ ከሚያደርሰው ጫና ባለፈ ተማሪዎች ትምህርታቸው እንዲያቋርጡ ይገደዱ እንደነበር እና ከዚህ በኋላ ግን ችግሩን እንደሚቀርፍ ተናግሯል።
የንጹህ መጠጥ ውሃው 70 ሚሊየን ብር የጨረሰ ሲሆን 4 ቀበሌዎች እና ለ 20 ሺ የማህበረሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ እንደሚያደርግ የገለጹት አቶ መብራቴ የወረዳው የውሃ ሽፋን ወደ 30 ፐርሰንት ይደግ እንጂ በወረዳው የንጹህ መጠጥ ውሃ ለህብረተሰቡ ለማዳረስ ገና ብዙ መስራት ይጠበቃል ነው ያሉት። ለዚህ ፕሮጀክት መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ምስጋናቸው አቅርበዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች እንደተናገሩት በዛሬው እለት የተመረቀው የካናስ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት በተለይ በእናቶች እና ተማሪዎች ላይ ይደርስ የነበረው ከፍተኛ እንግልት የሚቀንስ መሆኑን ተናግረዋል።
አክለውም ዉሃ ፍለጋ ብዙ እርቀት መንገድ በመጓዛቸው እና ንጽህና ያልተጠበቀ ውሃ በመጠጣታቸው ለበሽታ ይጋለጡ እንደነበር ነዋሪዎቹ አስታውቀዋል።
ለፕሮጀክቱ መጠናቀቅ አስፈላጊውን ድጋፍ ሲያደርጉ እንደነበር ያስታወሱት ሀሳብ ሰጪዎቹ አገልግሎቱ ለቀጣይ ትውልድ እንዲሸጋገር አስፈላጊውን ጥበቃ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *