የካቲት 14/2017 ዓ.ም
==========የእኖር ወረዳ ህብረተሰብ በመንገድ ልማት ዘርፍ በየአመቱ ከፍተኛ ተሳትፎ በማድረግ ታሪካዊ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን ተገለጸ።
የጉራጌ ዞን ትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ ሐላፊ ወ/ሮ ትብለጥ እስጢፋኖስ በእኖር ወረዳ በመንግስት እና በህብረተሰቡ ተሳትፎ እየተሰራ ያለው የመንገድ ግንባታ ተዟዙረው ተመልክተዋል።
ሐላፊዋ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት መንገድ ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥቅም እንዳለው አመላክቷል።
አርሶ አደሩ ባመረተው ምርት ላይ የገበያ ትስስር ለመፍጠር መንገድ ወሳኝ መሆኑንም ገልጿል።
ወ/ሮ ትብለጥ የህብረተሰቡ የመንገድ ልማት ተሳትፎ አስደሳችና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ተግባር መሆኑንም ጠቁሟል።
የእኖር ወረዳ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ጽ/ቤት ሐላፊ አቶ ተመስገን ኑርጋ በበኩላቸው የወረዳው ህብረተሰብ በመንገድ ልማት ዘርፍ በየአመቱ ከፍተኛ ተሳትፎ በማድረግ ታሪካዊ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን ገልጸዋል።
በየመድረኩና በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ በመንገድ ልማት ዙሪያ ለህዝቡ ግንዛቤ መፍጠር በመቻሉ ህብረተሰቡ ቁጭ ብሎ መንግስት ከመጠበቅ ይልቅ በተግባሩ ላይ በንቃት በመሳተፍ ልማቱ እያፋጠነ ይገኛል ብሏል።
በመሆኑም በበጀት አመቱ በወረዳው መንግስት፣በህብረተሰቡና ከተማ በሚኖሩ የአካባቢ ተወላጆች ተሳትፎ 52.4 ኪ/ሜ መንገድ ለመስራት ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን ገልጿል።
እስካሁን ባለው ከ36 ሚሊየን ብር በላይ ሃብት መሰብሰቡን የጠቀሱት አቶ ተመስገን 47 ኪ/ሜ የአፈር ስራ የተሰራ ሲሆን 25 ኪ/ሜ ገረጋንቲ የማቅረብ እና 15 ኪ/ሜ የመበተን ስራ የተሰራ መሆኑንም ጠቁሟል።
በፕሮግራሙ ላይ የጉ/ዞን የትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ ሐላፊ ወ/ሮ ትብለጥ እስጢፋኖስ እና ምክትል ሐላፊ ወ/ሮ መቅደስ ፣የወረዳው ት/መ/ል ሐላፊ አቶ ተመስገን ኑርጋ እና ምክትል ሐላፊ አቶ ጸጋዬ ይርጋን ጨምሮ የዞን ኮሚኒኬሽን ሚዲያ ባለሙያዎች ተገኝተዋል።
በዕለቱም በወንጬ፣በጋርዳሼ፣በከረቤድ፣በጃቱና በጎምሽ በመንግስትና በህብረተሰቡ ተሳትፎ እየተሰራ ያለው የመንገድ ግንባታ ተዟዙረው ተመልክተዋል። ዘገባው የወረዳው መ/ኮ ነው።




