የካቲት13/2017 ዓ.ም
==============
የጤና ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ለማሻሻል በትኩረት መስራት እንደሚገባ የእኖር ወረዳ ጤና ጽ/ቤት አስታወቀ።
ጽ/ቤቱ የ2017 በጀት አመት የ7 ወር ተግባር አፈፃፀም ግምገማ አካሄደ።
በግምገማ መድረኩ ባለፉት ወራት ውስጥ የተከናወኑ አበረታች ተግባራትን በማስቀጠል ጉድለቶችን ለይቶ ማረም እንደሚገባም ተመላክቷል።
የጽ/ቤቱ ምክትል ሀላፊ አቶ ቋሲም ፀጋዬ በመድረኩ ላይ ተገኝተው እንደገለፁት ጤና ለቤተሰብ፣ለማህበረሰብና ለሀገር ሁለንትናዊ እድገት መሠረት መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም በወረዳው ተላላፊ የሆኑና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች የመከላከልና የመቆጣጠር አፈፃፀም ከፍ ለማድረግ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
እንደ ሀላፊው ገለጻ በአሁን ወቅት በጤናው ዘርፍ እንደ ሀገረ ፈታኝ የሆነው የመድሀኒት አቅርቦት ችግር ለመፍታት ከወረዳው መንግስት ጋር በመሆን የተቻለውን ሁሉ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
አቶ ቋሲም አክለውም የአፈፃፀም ድክመት ያለባቸው የጤና ተቋማት፣የጤና ኤክስቴንሽኖች
፣ኄላፊዎችና ባለሙያዎች እራሳቸውን በመፈተሽ ማህበረሰቡን ሊመጥን የሚችል አገልግሎት ሊሰጡ ይገባል ብለዋል።
የ2017 በጀት አመት የ7 ወር ተግባር አፈፃፀም ሪፖርት በጽ/ቤቱ ልማት ዕቅድ በአቶ ዩኑስ ኤላያስ በኩል ቀርቦ ሀሳብና አስተያየት ተሰጥቶበታል።
አቶ ይኑስ በሪፖርታቸው የማዐጤመ ተጠቃሚነትን ማሻሻል፣ኤች አይ ቪ ኤድስ፣ የእናቶች ጤናን ማሻሻልና የህፃናት ሞትን መቀነስ፣የወባና የቲቪ በሽታ፣ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን መከላከልና መቆጣጠር፣የመንገድ ዳር ሽንት ቤት ግንባታ ስራዎች ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
በጤና ተቋማት ላይ የሚስተዋሉ የአገልግሎት አሰጣጥና የመድሀኒት አቅርቦት ችግር በመቅረፍ ለህብረተሰቡ ፍትሀዊና ጥራት ያለው አገልግሎት በመስጠት ሞዴል ቀበሌዎችና ጤና ጣቢያዎች ለመፍጠር እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በሪፖርቱ የነፍሰጡር እናቶች የወሊድ ክትትል በጤና ተቋማት በተቀመጠው አሰራር መሰረት እንዲተገበር በማድረግ የህፃናትና የእናቶች ሞት ለመቀነስ እየተሰራ ያለው ስራ ይበልጥ መጠናከር እንዳለበትም አመላክተዋል።
የጤና ተቋማት አካባቢ የመረጃ አያያዝና ጥራት ላይ ችግሮች መኖራቸውን ያነሱት አቶ ዩኑስ ባለሙያዎች በቀጣይ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ አሳስበዋል።
አንዳንድ የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት በቀጣይ በሁሉም የጤናው ዘርፍ የነበሩ ጉለቶች በማረም ጥራት ያለውና ፍትሀዊ አገልግሎት ለመስጠት በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
በግምገማ መድረኩም የወረዳውጤና ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ቋሲም ፀጋዬ፣የጽ/ቤቱ ባለሙያዎችና እንደዚሁም የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ተገኝተዋል ሲል የዘገበው የወ/መ/ኮ/ጉ/ጽ/ቤት ነው።


