መስከረም 15/2017 ዓ.ም
================
ጉራጌ ሊመረቅ ወደ ትውልድ ቀዬው ገብቷል።
የጉራጌ ተወላጅ ከህይወት ዋና ግቡ መካከል አንዱ በቤተሰቡ መመረቅ ነው።ምርቃት ቢከፋም ቢደላም መፅናኛ ነው።የጉራጌ ልጅ የቤተሰቦቹ ምርቃት የስኬቱ መንገድ አድርጎም ያየዋል።
ለዚህ ነው ከትውል አካባቢው ርቆ የሚኖረው የጉራጌ ተወላጅ ባለው አቅም ቤተሰቦቹን ለማስደሰት በዓመት መስቀል ወይም አረፋ ወደ ትውል ቀዬው የሚተመው። ቀዬው ሲደርስም በወላጆቹና በዘመድ አዝማዱ ምርቃት መንፈሱ በእርካታ ያረሰርሳል።
እናት መቀነታቸውን ፈተው ከልብ በመነጨ የደስታ ሲቃ እየተናነቃቸው ልጆቻቸውን ይመርቃሉ። አባት የተገዛውን ሰንጋ ሻኛ እየዳበሱም “ዴንጎ ተራኡዋ፣ ከተማ በየ አሁዋ” ልጆቼ እደጉም ተመንደጉም ብቻ ሳይሆን ከተማ ይመቻችሁም ይላሉ። መጥፎውን ያርቅላችሁ፤ምቀኛም ይሁን ሸረኛ ይያዝላችሁ..ሌላም ሌላም እያሉም ይመርቃሉ። ብቻ የበረከት መልካም ምኞታቸውን ከልብ ይገልጹላቸዋል።
አያት የጋቢያቸው ጥለት እየቋጩም እንደዚህ ክበዱ፣ ውለዱ፣እንደ ጥለቱ ዘራቹህ ይብዛ፤ሀብታችሁ ይትረፍረፍ፤ እድሜ ከጤና ጋር አሟልቶ ይስጣቹህ እያሉም ይመርቃሉ።
አባት ለልጆቹ ለልጅ ልጆቹ በወላጆቹ የተመረቀ መሆኑን ምርቃት በትውልድ ቅብብሎሽ እንደሚሰራም ያስረዳቸዋል።በዝያው ልክ የእርግማን መጥፎነት ይነግራቸዋል።
ለመስቀል ሀገሩ ያልገባ ጉራጌ በእለቱ ይከፋል፤ይተክዛል፡፡ላለመቅረትም ቃል ኪዳኑን ያድሳል። ልጃቸው ለመስቀል ያልመጣላቸው ወላጆችም የፈለገ ሰንጋ ቢጥሉ ቤቱ ሞልቶ ቢትረፈረፍ እንኳ በልጆቻቸው መቅረት ይከፋሉ። የጉራጌ አባትና እናትም ለወራት የናፈቋቸው ልጆቻቸውን በበዓል ወቅት የማግኘት ያክል የሚያስደስታቸው ነገር የለምና።
መስቀል ወይም አረፋ ወደ ሀገር ቤት መግባት ከመንፈሳዊ ፋይዳው በተጨማሪ የአስተሳሰብ እድሳት፣ የአዲስ እቅድ ጅማሮ ፣ የስኬት መንደርደርያ ፣ የጋብቻና የመብዛት ነፀብራቅ ተደርጎም ይታያል። ጉራጌ በዓመት በአል መንፈሳዊና ቁሳዊ እፎይታ የሚያገኝበት እድሉ ነው።
ለመስቀል ወይም ለዓረፋ ከተሞች ጭር ቢሉ አትገረሙ። ጉራጌ ሊመረቅ ወደ ትውልድ ቀዬው ገብቷል። ጉራጌ ሲመረቅ ኢትዮጵያ ትባረካለች ።በመስቀል ዕለት ልጅና አዋቂ አዲስ ልብስ ለብሶ ለቤቱ አዲስ ጅባ ወይም ምንጣፍ ተነጥፎና ተጎዝጉዞም አካባቢው ይደምቃል።
ሰንጋ ሲታረድም ይሁን ክትፎ ሲበላና ቡና ሲጠጣም ይሁን ሌላም ሌላም ኢትዮጵያ ሀገራችን ዳር ድንበሯ ሰላም ይሁን፣ትበልፅግ፣ ጠላቶችዋ ይውደሙ…ሳይባል ቀርቶ አያውቅም። በጉራጌ ውስጥ እንዲህ በየሁነቱ ኢትዮጵያዊነትን በደማቁ ጎልቶም ይታያል።እኛም ምርቃት በጉራጌ ምን እንደምታ አለው? የሚለውን በጥቂቱ ልናስቃኛችሁ ወደድን ሰላም!
ወሄ ሙርኣ ኧህር
መልካም የመስቀል በአል!!
እያለ የእኖር ወረዳ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት መልካም ምኞቱን ይገልጻል!





+8