ህብረተሰቡ ሁሉ አቀፍ የጤና አገልግሎት በፍትሀዊነት እንዲያገኝ በቀረው አጭር ጊዜ ውስጥ ሁሉም የማዐጤመ አባል ማድረግ እንደሚገባ የእኖር ወረዳ አስተዳዳር አሳሰበ

የካቲት 25/2017 ዓ.ም
****************ህብረተሰቡ ሁሉ አቀፍ የጤና አገልግሎት በፍትሀዊነት እንዲያገኝ በቀረው አጭር ጊዜ ውስጥ ሁሉም የማዐጤመ አባል ማድረግ እንደሚገባ የእኖር ወረዳ አስተዳዳር አሳሰበ።
የእኖር ወረዳ ጤና ጽ/ቤት የሁሉም ቀበሌዎች እስከ የካቲት 24/2017 ዓ.ም ድረስ የማዐጤመ አፈፃፀም የደረሰበት ደረጃ አጠቃላይ የወረዳ እና የቀበሌ አመራሮች በተገኙበት በመገምገም የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል።
የእኖር ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መብራቴ ተክሌ በመድረኩ ላይ ተገኝተው እንደገለፁት ዜጎች ባላቸው የኢኮኖሚ ደረጃ ሳይሆን በህመማቸው ልክ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ከሚሰሩ ስራዎች አንዱ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሉት መሆኑን ተናግረዋል።
ለመዐጤመ አገልግሎት ከማህበረሰቡ የሚሰበሰበው ገንዘብ እጅግ በቂ አለመሆኑን አስረግጠው የተናገሩት ዋና አስተዳዳሪው ለሕዝቡ ሲባል የወረዳው መንግስት እንደ አንድ የካፒታል ፕሮጀክት አሰፈላጊውን ድጎማ እያደረገ መሆኑንም አስረድተዋል።
ህብረተሰቡ ሁሉ አቀፍ የጤና አገልግሎት በፍትሀዊነት እንዲያገኝ በቀረው አጭር ጊዜያት ሁሉም የማዐጤመ አባል ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል።
የወረዳው የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ሞሸዲን አህመድ እንደገለፁት የማዐጤመ አፈፃፀም በማሻሻል ህብረተሰቡ ፍትሀዊ የጤና አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበት ገልፀዋል።
ማዐጤመ ላይ ዝቅተኛ አፈፃፀም መኖሩን ያነሱት የመንግስት ዋና ተጠሪው ዘርፉ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይጠይቃል ብለዋል።
የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የአገልግሎት አሰጣጥ እና የመድሀኒት አቅርቦት እጥረት ላይ የሚስተዋሉ ውስንነቶች ለማረም እየተሰራ መሆኑንም ጨምረው ገልፀዋል።
ለዚህም የማዐጤመ አገልግሎት ተደራሽነት ለማስፋት እንደዚሁም በአጭር ጊዜ ውስጥ አዳዲስ አባላትን ለማፍራት የአመራርና የፈፃሚ ቁርጠኝነት ወሳኝ በመሆኑ ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበትም አቶ ሞሸዲን አጽንኦት ሰጥተዋል።
የወረዳው ጤና ጽ/ቤት ሀላፊ ወ/ሮ ብርዝነሽ ባደታ በበኩላቸው በቀረው አጭር ጊዜያት ውስጥ የወረዳና የቀበሌ አመራሮች፣ የጤና ባለሙያዎች አዲስ አባላት በማፍራት፣መታወቂያ በማደስ፣ደረሰኝ በወቅቱ በማስገባትና ገንዘቦችን በወቅቱ ወደ ቋት በማስገባት ረገድ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
ሀላፊዋ አክለውም ቀሪ ያልተዳሰሱ እና ገቢ ያልተደረጉ ዝቅተኛ አፈፃፀም ያላቸው ቀበሌዎች የተሻለ አፈፃፀም ካላቸው ቀበሌዎች ተወዳዳሪ ለማድረግ በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላት በባለቤትነት መስራት እንዳለባቸው አመላክተዋል።
መክፈል የማይችሉ አባላት ልየታ ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ በማድረግና ሀብት ማፈላለግ ላይ አማራጮችን በተገቢው በመጠቀምና ከፋይ አባላት ብዛት 100% ከፍ በማድረግ የመንግስትን ጫና ለመቀነስ መስራት ይገባል ነው ያሉት።
በመድረኩ ከተገኙት ባለድርሻ አካላት መካከል አቶ ፍቅሬ መልስ፣አቶ ፈድሉ ሁሴን እና አቶ ኮሩ መርስነህ ሶስቱም በጋራ በሰጡት አስተያየት ማዐጤመ ለማህበረሰቡ ወሳኝና አስፈላጊ በመሆኑ የደረሰኝ አያያዝና ሌሎችም ላይ የሚስተዋሉ የአሰራር ክፍተቶችን ለማረም መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
በግምገማው ላይ የወረዳና የቀበሌ አመራሮችን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል
 

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *